ታኀሳስ ፲፫ (አስራ ሦስት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-በኢትዮጵያ የተከሰተውን ረሃብ በመሸሽ እንዲሁም የመንግስትን የማዳበሪያ እዳ ለመክፈል ሲሉ በርካታ አርሶደሮች ወደ አዲስ አበባ እየተሰደዱ ሲሆን፣ አርሶ አደሮቹ በተለይም ዘነበወርቅ በሚባለው ቦታ ሰፍረው እንደሚገኙ ታውቋል።
የ7 ልጆች አባት የሆኑት አርሶአደር ከጎጃም ተሰደው መምጣታቸውን ይናገራሉ። መነኩሴ እናታቸው ይዘው መምጣታቸውን የሚገልጹት አርሶ አደሩ በረሃቡና በማዳበሪያ እዳ ምክንያት እርሳቸው እና ሌሎች በርካታ አርሶአደሮች ተሰደው መምጣታቸውን ገልጸዋል። የቁጠባ ብር ብንበደርም ያንን ለመክፈል አልቻልም ሲሉ አርሶአደሩ ተናግረዋል
ከመቀሌ የመጡ ሁለት በእድሜ ገፉ ሰዎች ደግሞ በርሃብና በማዳበሪያ እዳ የተነሳ መሰደዳቸውን ተናግረዋል። የማዳበሪያ እዳ ካልከፈልን እንታሰራለን ያሉት አንደኛው አባት፣ ከረሃቡ በላይ ውሃ መጥፋቱም እንዲሰደዱ እንዳደረጋቸው ገልጸዋል ።
አንድ በእድሜ የገፉ ከትግራይ የመጡ እናት “ረሃብ ክፉ ነገር በመሆኑ ተሰደድኩ” ብለዋል። የአለማቀፍ ድርጅቶች በዚህ አመት በተከሰተው ድርቅ 16 ሚሊዮን የሚጠጉ ኢትዮጵያውያን እንደሚራቡ በመግለጽ ላይ ናቸው።
ይህ በእንዲህ እንዳለ በአዋሳ ከቤት መፍረስ ጋር በተያያዘ በርካታ ነዋሪዎች ለጎዳና ህይወት መዳረጋቸውን ዘጋቢያችን በፎቶ አስድግፎ የላከው መረጃ ያመለክታል።
ምንም እንኳ ተፈናቃዮች ከመንግስት የሚደርስባቸውን ጫና በመፍራት በቪዴዮ ለመቀረጽ ባይፈልጉም፣ ለጎዳና ህይወት የተዳረጉት መንግስት ቤታቸውን ስላፈረሰባቸው መሆኑን ገልጸዋል።