የማምረቻ እንዱስትሪዎች በዶላር እጥረት ለቅሶ ላይ ነን ሲሉ ባለሀብቶች ተናገሩ
( ኢሳት ዜና ሃምሌ 17 ቀን 2010 ዓ/ም ) በኢትዮጵያ የማምረቻ እንዱስትሪ ባለሀብቶች ከአዲሱ የብሄራዊ ባንክ ገዢ ከአቶ ይናገር ደሴ ጋር ባደረጉት ውይይት እንደገለጹት የውጭ ምንዛሬ እጥረት እንዲሁም ያለውን የውጭ ምንዛሬ ቅድሚያ ለውጭ ባለሀብቶች መሰጠቱ ከፍተኛ ጉዳት እያመጣባቸው ነው።
የሲዲኤፍ ቢዝነስ ግሩፕ ባለቤት 800 ሰራተኞችን ቢያስተዳድሩም፣ ወደ አምራች እንዱስትሪ የገቡበትን ቀን እየረገሙ እንደሚገኙ ገልጸዋል።
የብረታብረት አምራች ድርጅት ወኪል የሆኑት ግለሰብ ደግሞ 3800 ሰራተኞች እንዳላቸው ይናገራሉ። መንግስት ካወጣው ህግ አንጻር እራሱን ራሱን መፈተሽ አለበት የሚሉት ወኪሉ፣ ብሄራዊ ባንክ በሚከተለው የተዛባ አሰራር ችግር ውስጥ መግባታቸውን ተናግረዋል።
ሌላው ባለሀብት ደግሞ በአለም ላይ እንድንወዳደር የሚያስችሉን የመሰረተ ልማቶችና የገንዘብ አቅርቦት ሳይኖር፣ ምርት ወደ ውጭ ላኩ መባላችን ከማምረቻ እንዲስትሪው እንድንወጣ እየገፋን ነውይላሉ።
የዋሊያ ብረታ ብረት እንዱስትሪ ባለቤት በኩላቸው በእርሳቸው የስራ ዘረፍ የተሰማሩ የውጭ ባለሀብቶች ወይም ከእነሱ ጋር የሚሰሩ ሌሎች ባለሀብቶች የውጭ ምንዛሬ ሲያገኙ እነሱ የአገር ውስጥ ባለሀብቶች በመሆናቸው ብቻ ለአንድ አመት ተኩል ያክል የውጭ ምንዛሬ ለማግኘት አለመቻላቸውን ገልጸዋል።
አንድ ባለ 5 ኮከብ ሆቴልና አንድ ፋብሪካ አለኝ የሚሉት ባለሀብት ደግሞ በውጭ ምንዛሬ እጥረት ሰራተኞችን ለመቀነስ መገደዳቸውን ተናግረዋል።
የብሄራዊ ባንክ ገዢ ዶ/ር ይናገር ደሴ ለተነሱት አስተያየቶች በሰጡት መልስ በመጀመሪያው ትራንስፎሜሽን እቅድ የስኳር ፋብሪካ ገንብተን የውጭ ምንዛሬ እናገኛለን ብለን ብናስብም አይደለም በመጀመሪያው እቅድ፣ አሁንም በያዝነው ሁለተኛው እቅድም አልደረሰም ብለዋል። ከግብርና፣ ከማንፋክቸሪንግና ከወርቅም የምናገኘው የውጭ ምንዛሬም የለም በሚባልበት ደረጃ ላይ ደርሷል በማለት ዶ/ር ይናገር ተናግረዋል።