ሰኔ ፳፫ ( ሃያ ሦስት ) ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- ካለምንም ሕጋዊ ቪዛ በሕገወጥ መንገድ ወደ ማላዊ ገብታችኋል በተባሉ 27 ስደተኞች ላይ እያንዳንዳቸው 20 ሽህ የማላዊ ክዋቻ እንዲከፍሉ ሲል የአገሪቱ ከፍተኛው ፍርድ ቤት በየነ። ከተፈረደባቸው ስደተኞች ውስጥ ከአንዱ በስተቀር የተቀሩት ሃያስድስቱም በሙሉ ኢትዮጵያዊያን ስደተኞች ናቸው።
ስደተኞች ማክሰኞ እለት በሕገወጥ መንገድ በአንድ ተሽከርካሪ ላይ ተጭነው ሲጓዋዙ ይጠቀሙበት ከነበረው ተሽከርካሪ ጋር በካራንጋ አውራጃ በፖሊስ ክትትል መያዛቸውን የአካባቢውን ባለስልጣናት ጠቅሶ ማራቪ ፖስት መዘገቡ ይታወሳል። የጭነት መኪናው ባለቤት የዶዋ አውራጃ ነዋሪ የሆኑት የአቶ አመዲ ሃሰን እንደነበርም በክሱ ላይ ተገልጿል።
ኢትዮጵያዊኑ ከውሳኔው በኋላ ከዚህ በፊት ምንም ዓይነት የወንጀል ተግባር ላይ አለመሰማራታቸውን እና ለስድስት ወራት በቂ ምግብ አለማግኘታቸውን በመጥቀስ ፍርድ ቤቱ ይህንን ከግምት ውስጥ በማስገባት የቅጣት ማቅለያ ምህረት እንዲያደርግላቸው ተማጽኖዋቸውን አሰምተዋል።
የቀጠናው ፖሊስ ጣቢያ ረዳት ኢንስፔክተር ኬልቪን ካማንጋ በበኩላቸው ”ስደተኞቹ ከዚህ በፊት በማንኛውም ወንጀል ላይ አባይሳተፉም የአገሪቱን ድንበር በመጣስ በሕገወጥ መንገድ ባልተለመደ መግቢያ በመግባታቸው ሊቀጡ ይገባል” ሲሉ ለፍርድ ቤቱ ተናግረዋል።
የሕገወጥ ስደተኞች መቅጫ አንቀጽ 141ን በመተላለፍ ከተሽከርካሪ ጋር አንድ ላይ በመያዛቸው ጠንከር ያለ ቅጣት ሊቀጡ ይገባል ሲል አቃቤ ሕግ የቅጣት ማቅለያውን ተቃውሟል።
ፍርድ ቤቱም የከሳሽ አቃቤ ሕግን እና የተከሳሽ ኢትዮጵያዊያንን የቅጣት ማቅለያ ካዳመጠ በኋላ እያንዳንዳቸው 20 ሽህ የማላዊ ክዋቻ እንዲከፍሉ እና እጅ ከፍንጅ የተያዘው መኪና ለመንግስት ገቢ እንዲሆን ሲል ብይን መስጠቱን ማራቪ ፖስት አክሎ ዘግቧል።