የማህበራዊ ሚዲያዎች ለፖለቲካ ተቃውሞ ዋነኛ ምህዳር ሆነዋል ተባለ
ግንቦት ፳፱(ሃያ ሃያ ዘጠኝ) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ “ሶሻል ሚዲያ ለፀጥታ እና ለብሄራዊ ደህንነት አገልግሎት ያለው ፋይዳ እና የምንከተለው ስትራቴጂ “ በሚል ለጸጥታ ሃይሎች ባዘጋጀው ሰነድ ላይ “ ማህበራዊ ድረገጾችን በመጠቀም የሚደረግ የመረጃ ልውውጥ ተፈላጊነት እንቅስቃሴ በከፍተኛ ሁኔታ መጨመሩ ፣ የልማታዊ መንግስት ግንባታ እንቅፋቶች የሆኑትን ጠባብነት ፣ ትምክት፣ አክራሪነት ወይም ጽንፈኝነት፣ ኪራይ ሰብሳቢነት እና ሽብርተኝነት ማስፋፊያ መሳሪያ ሆነዋል” በመላት በመንግስት ላይ የደቀኑትን አደጋ ዘርዝሯል።
የመንግስት የጸጥታ ሃይሎች መከተል ስላለባቸው የማህበራዊ ሚዲያ አጠቃቀም በሚዘረዝረው በዚህ ሰነድ ላይ “ወንጀል ነክ ብሎም ከሃር ሰላም እና ደህንነት ጋር የተያያዙ በማህበራዊ ሚዲያ የሚሰራጩ መረጃዎች እና ስነልቦናዊ ዘመቻዎች በመበራከታቸው ለቁጥጥር አስቸጋሪ እየሆነ መጥቷል” ብሎአል።
ማህበራዊ ሚዲያው የኒዮ ሊበራል ሃይሎች አፍራሽ ዘመቻ እንቅስቃዎች አውድማ መሆኑ ብቻ ሳይሆን ለፖለቲካ ተቃውሞ ዋነኛ ምህዳር ሆኗል ይላል።
“በመካከለኛው ምስራቅ፣ አረብ ሃገራት እና በሰሜን አፍሪካ ማለትም በቱኒዚያ፣ ሶሪያ፣ ግብጽ፣ ሊባኖስ በ2011 በተነሳው አመጽ የማህበራዊ ሚዲያው የነበረው አስተዋጽኦ ከፍተኛ መሆን፣ አገራቱ ይህን ሚዲያ እስከመዝጋት እንዳደረሳቸው” የሚተነትነው ሰነዱ፣ በኢትዮጵያ ውስጥም እየፈጠረ ስላለው ተጽእኖ ያብራራል።
በኢትዮጵያ ውስጥ እስከ ግንቦት 2007 ዓም ድረስ 3 ሚሊዮን ኢንተርኔት ተጠቃሚዎች መኖራቸው፣ የፌስ ቡክ ተጠቃሚው ብዛት 1 ሚሊዮን 600 ሺ መድረሱን ፣ በእድሜ ደረጃ ሲታይም 80 በመቶ የሚሆኑት ከ18-34 ባለው የእድሜ ክልል እንደሚገኙ እንዲሁም 75 በመቶ የሚሆኑት ወንዶች መሆናቸውን ይገልጻል።
በኢትዮጵያ ያሉ ማህበራዊ ሚዲያዎች “ልማታዊ መስመር የሚከተሉ “ እና “አፍራሽ መስመር የሚከተሉ” ተብለው በሁለት እንደሚከፈሉ የሚገልጸው ሰነዱ፣ ልማታዊ መስመር የሚከተሉት “ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን፣ ኢትዮጵያ ሬዲዮና ቴሌቪዥን፣ የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ ኢፒአርዲኤፍ ኦፊሻል፣ የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ የህዝብ ግንኙነት ፣ የኢትዮጵያ ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች መስሪያ ቤት” መሆናቸው ሲጠቅስ፣ አፍራሽ መስመር ይከተላሉ የተባሉት ደግሞ “መረጃ ዶት ኮም፣ ኢሳት፣ ኢካዲኤፍ፣ ጎልጉል ድረገጽ፣ ድምጻችን ይሰማና ነገረ ኢትዮጵያ “ ናቸው።
አፍራሽ ሚዲያዎች “የፖሊስ ሀይሉን ጨፍጫፊ አስመስሎ በማቅረብ ህብረተሰቡ በጠላትነት እንዲፈርጀው እና ከህብረተሰቡ እንዲነጠል ሁኔታዎችን እንደሚያመቻቹ፤ በመንግስት ውሳኔዎች እና ህጎች ዙሪያ የሚነሱ ርዕዮተ-ዓለማዊ ጭፍን ተቃውሞዎችን እንደሚያራምዱ፤ የመንግስት ግልበጣ፣ የአመፅቅስቀሳዎች ፣ ዘረኝነት እና የሀይማኖት አክራሪነት እንዲሁም ከአፈፃፀም ጋር በተገናኘ የሚነሱ ከሃይማኖትና ከብሄር ጋር የተያያዙ ቅሬታዎች እንደሚያባብሱ” ይገልጻል። “ የመንግስትን ደካማ ጎን የሚሏቸውን ጉዳዮች አጉልቶ በማሳየት በአሉታዊ መፈረጅ እና ማስፈረጅ፣ ዓለም አቀፍ የዲፕሎማሲ ግንኙነቶችንእና የአገርን ገጽታ የሚያጠለሹ ጽሁፎችን መጻፍ፤ የመንግስት ባለስልጣናት በሙስናና በብልሹ አስተዳደር የሚከሱ ወቀሳዎችን ማቅረብ፣ ከስርዓቱ ጋር መልካም ግንኙነት ያላቸውን ታዋቂ ግለሰቦችና ተቋማት የሚያጠለሹ ጽሁፎችን መልቀቅ፣ መንግስትን እና የፀጥታ አካላቱን በሰብዓዊ መብት የሚከሱ እናየሚያጥላሉ እንዲሁም ምርጫ ተከትሎ ህብረተሰቡን የማመስ፣ለሁከት እና ብጥብጥ ለማነሳሳት ግፊት ለማድረግ በመሳሪያነት መጠቀም፣ ብጥብጦች እና አሉባልታዎችን የሚያጭሩ አጀንዳዎችን በምህዳሩ ላይ በማሰራጨት በህብረተሰቡ አለመረጋጋት እንዲፈጠር ማድረግ፣ ህብረተሰቡ ከሰላማዊ ትግልይልቅ የጎዳና ላይ ነውጥ እንዲከተል የሚያደርጉ አፍራሽ አጀንዳዎችን በማሰራጨት አገሪቱን አዘቅት የማስገባት ስትራቴጂ” ይከታተላሉ ተብለዋል።
“የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች በSMS፣በፌስቡክ አካውንታቸው ወይም በሽብር ቡድኖች ልሳኖች ተጠቅመው አሉታዊ መግለጫ እንዲሰጡ በማድረግ የእርስ በርስ ግጭት እንዲፈጠር በማድረግ ክፍተቱን የመጠቀም ፍላጎት “ እንዳላቸውም ተጠቅሷል።
አንድ የመንግስት ጸጥታ ሃይል የአፍራሽ ሀይሎች መሳሪያ ተጠቂ ሆኗል ብሎ ለመናገር የሚከተሉትን ባህሪያት ማሳየት አለበት ይላል ሰነዱ፦
“የሽብር ሀይሎችን አፍራሽ የሶሻል ሚዲያ እንቅስቃሴዎች ተቀብሎ ለሌሎች ማስተላለፍ፣ ለምሳሌ በሞባይል ብሉቱዝ መላላክ፣የፌስቡክ አካውንቶችን ተጠቅሞ ለሌሎች ሸር በማድረግ ( ማካፈል)፣በአሉባልታ፣በጨዋታ እና በሌሎች ተመሳሳይ ማስፋፊያ ዘዴዎችን መጠቀም፣ የሽብር ሀይሎችን ገጾች፣የፌስ ቡክግሩፖች፣እና የተቃዋሚ አክቲቪስቶች አካውንት እና ፔጆች ላይክ፣አድ ማድረግ የኛ ተከታዮችም መረጃው እንዲደርሳቸው ስለሚያደርግ ወንጀል መሆኑ፣ የአፍራሽ ሀይሎችን አስተሳሰብ የሚያስፋፉ መረጃዎችን በሞባይላችን ይዘን ከተገኘን እና የዚህ አፍራሽ አስተሳሰብ ሰለባ ከሆንን፣ የፌስ ቡክአካውንታችንን ደህንነት ማስጠበቅ የማንችል እና የማንቆጣጠር ከሆነ ፕሮፋይላችን ለአፍራሽ ሀይሎች ማስተላለፊያ መሳሪያ የሚሆን ከሆነ በኛ ዘንድ የሚገኙ ሚስጥራዊ እና አንገብጋቢ መረጃዎች ተወስደው ባልሆነ መንገድ ማህበራዊ ሚዲያ ላይ በማህበረሰቡ ዘንድ አሉታዊ ትርጉም ሲፈጥሩ እንዲሁምየአፍራሽሀይሎችን አጀንዳ በማወቅም ባለማወቅም ስናስተላለፍ ብሎም ከአነስተኛ የአጠቃቀም እውቀት የተነሳ ሌሎች እኛ ገፅ ላይ የማንፈልጋቸውን መልእክቶች ሲያጋሩ ያኔ የጸጥታ ሃይሎ በአፍራሽ ሃይሎች ተጠቅተዋል” ማለት እንደሚቻል ይናገራል።
የመንግስት የጸጥታ ሃይሎች በአፍራሽ ሃይሎች በቀላሉ የሚጠቁት ፣ ቴክኖሎጂውን በእውቀት ላይ በተመሰረተ መልኩ ሳይጠቀሙ ሲቀሩ፣ ሳይበሩ ላይ ለሚታዩ ነገሮች በቀላሉ ሲማረኩና አነስተኛ የቴክኖሎጂ እውቀት ሲኖራቸው ነው የሚለው ጽሁፉ፣ በመንግስት የጸጥታ ሃይሎች የሚታየውን ችግር ለመቅረፍ መንግስት እና የጸጥታ ሃይሎች “ የአባላቱን የሶሻል ሚዲያ አጠቃቀም ቴክኒካል ከህሎት ማሳደግ ፣ ጠንካራ የኢንፎርሜሽን እና የኮምንኬሽን ስራ በመስራት የማህበረሰብ ንቅናቄ መፍጠር፣ ሽብርተኝነትን የሚያስፋፉ አጀንዳዎችን ተቀብሎ ማስተጋባት ከህገ-መግስቱ እና ፀረ-ሽብር አዋጁ ጋር የሚፃረር መሆኑን ማስገንዘብ ፣ በክህሎት፣በአውቀት እና በአመለካከት የሰለጠነ ሰራዊት መገንባት” እንደሚያስፈልግ ይመክራል። “ እራሳችንን በእውቀትና በመረጃ ማዳበር/መገንባት ፣ የምንሰጠውን/የምናወጣውን መረጃ ጠንቅቆ ማወቅ፣ መረጃ ሲጠየቁ ፈጥኖ ምላሽ ከመስጠት መቆጠብ ፣ ህግ መንግስቱን ኢንተርናላይዝድ በማድረግ የስራ መመሪያ ማድረግ ፣ ሚስጥራዊ መረጃ ለሶሻል ሚዲያ አገልግሎት አለማዋል ፣ የስጋት ሀይሎችን ገፆች ላይክ አለማድረግ (መሳሪያ አለመሆን)” የሚሉት ምክሮችም የጸጥታ ሃይሉን ከማህበራዊ ሚዲያዎች ተጽእኖ ማላቀቂያ መንገዶች መሆናቸው ተመልክቷል።
ከጸጥታ ጋር በተያያዘ ስራ የሚሰሩ ወታደሮች በተቻላቸው መጠን ራሳቸውን ከማህበራዊ ሚዲያ እንዲያርቁ ካልሆነም የአጠቃቀም ክህሎታቸውን እንዲያሳድጉ ያ ሳይሆን ሲቀርና መረጃዎችን ሲያሰራጩ በወንጀል መጠየቅ እንዳለባቸውም ይገልጿል።
የኢሳት ምንጮች እንደገለጹት አብዛኛው የጸጥታ ሃይሎች በተለይም ፖሊሶችና የደህንነት ሰራተኞች ከፍተኛ የማህበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚዎች ናቸው። በእየለቱ የሚወጡ መረጃዎችን በንቃት እንደሚከታተሉና ስማቸውን በመቀየር አስተያየቶችን ሳይቀር እንደሚሰጡ ይናገራሉ። የሰራዊቱ ማህበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚነት መጨመር ያሰጋው መንግስት ከወራት በፊት ባደረገው ፍተሻ የአፍራሽ ሃይሎችን ጽሁፎች ወይም ፎቶዎች ያሰራጩ ወይም በሞባይላቸው አስቀምጠው የተገኙ ባላቸው ፖሊሶች እና የደህንነት ሃይሎች ላይ እርምጃ በመውሰድ ከ200 በላይ የፌደራል ፖሊስ አባላትን ከማባረሩ በተጨማሪ የተወሰኑት አስሯል።
2016-06-06