ነኅሴ ፳፮ (ሀያ ስድስት) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-ድርቁ ባስከተለው ጉዳት ምክንያት የሚመገቡት ባለመኖሩ አብዛኛው ወጣቶች ወደ ጠረፍ ከተማ በመሰደድ ላይ ናቸው።
በሰሜን ወሎና ዋግ ኽምራ ዞን ያሉ ነዋሪዎች በድርቁ ምክንያት እንስሳት አልቀዋል፤ መሬት የሌላቸው ወጣቶች የቀን ስራ በመስራት ቤተሰቦቻቸውን ለማገዝ ምግብ ፍለጋ ወደ ጠረፍ ከተማ እየተሰደዱ ነው።
መሬት የሌላችው ወጣቶች በየአካባቢያቸው መሬት ተከራይተው በማምረት ቤተሰቦቻቸውን ያስተዳድሩ እንደነበር የሚገልጹት አርሶ አደሮች፤ ዛሬ ከዝናቡ መዘግየት ጋር ተያይዞ እንደ በፊቱ መሬት ተከራይተው ለመስራት ባለመቻላቸው አካባቢውን ትተው በመጓዝ በቀን ስራ ራሳቸውን ለመደጎም ጥረት ያደርጋሉ። ወጣቶቹ የቤተሰባቸውን ሕይወት ለማቆየት እንደ አማራጭ የወሰዱት ወደ ጠረፍ ከተሞች በመሄድ በቀን ስራ ገንዘብ ማጠራቀም በመሆኑ አብዛኛው ወጣት ወደ መተማና ሱዳን እየተጓዙ ነው።
‹‹ በየአካባቢው ድርቅ በመኖሩ እዚህ ቁጭ ብለን ከምናይና የምንመገበው አጥተን ከምንቸገር መሄድ አለብን፡፡ ›› የሚሉትን ወጣቶች፣ አባቶች ‹‹ ችግራችንን በጋራ እዚሁ እንወጣው ›› በማለት ቢመክሩም ከመሄድ ለማስቀረት እንዳልቻሉ የችግሩ ሰለባ የሆኑት አርሶ አደሮች ተናግረዋል፡፡
በአሁኑ ሰዓት ቀደም ብሎ ተዘርቶ የነበረው የጤፍ ምርት ያለ ዝናብ በመቆየቱና አልፎ አልፎ በሚያገኘው ዝናብ አረሙ ገንፍሎ በመውጣት ምርቱን ከጥቅም ውጭ በማድረጉ፤ በቀጣዩ አመት ከፍተኛ የምግብ እጥረት እንደሚከሰት የአካባቢው አርሶ አደሮች ስጋታቸውን ያስቀምጣሉ፡፡
በድርቁ ምክንያት ተስፋ መቁረጣቸውን የሚናገሩት አርሶ አደሮች ድርቁ እየተባባሰ መምጣቱን ተናግረዋል፡፡ከተከዜ በኋላ ባሉት ቀበሌዎች በአብዛኛው ዝናብ ባለመኖሩ በመኸሩ ምንም ዓይነት ምርት አለማግኘታቸውን የገለጹት ተጎጂዎች፣ ችግሩን ገዢው መንግስት ቢያውቀውም እስካሁን ያደረገላቸው እገዛ እንደሌለ በቅሬታ ይገልጻሉ።
ባለፈው ዓመት በመኸር ስድስትና ሰባት ኩንታል ምርት እያንዳንዱ አርሶ አደር ማግኘቱን የሚገልጹት አንድ አርሶ አደር፣ ቀደም ብል ተዘርቶ የነበረው የጤፍ ምርት እንደገና በመገልበጥ ቢዘራም ወቅቱ ባለመሆኑ ውጤት እንደማይሰጣቸው ተናግረዋል፡፡፡
‹‹ በነሃሴ ወር እንዲህ አይነት ጸሃይ ሊኖር አይገባም ነበር፡፡ ›› የሚሉት አስተያየት ሰጪ፣ እንስሳት የሚመገቡት አጥተው ወደ ሞት ሲቃረቡ የአካባቢው አመራሮች ከህዝቡ የቀረበላቸውን ጥያቄ በማስተናገድ በከተሞች ዙሪያ ክልል ተራሮች ላይ የነበረውን የተከለከለ ሳር ታጭዶ እንስሳቱ እንዲመገቡት በመደረጉ እንስሳቱ ከጊዜያዊ እልቂት መዳናቸውን ተናግረዋል፡፡
በአሁኑ ሰዓት በገበያ ላይ ከብት የሚሸጥ እንጅ የሚገዛ አይታይም የሚሉት አርሶአደሩ፣ የአካባቢው ነዋሪዎች ከብት ቢገዙም ሳር ባለመኖሩ ሁሉም አርሶአደር ከብቱን በመሸጥ ላይ መሆናቸውን ይናገራሉ፡፡ ከአሁን በፊት እስከ ስምንት ሺህ ብር የሚሸጥ በሬ በአራትና አምስት ሺህ ብር እየተሸጠ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡
ህብረተሰቡ ከብቶቹን አርዶ ለመብላት እንደሚገደድ የሚናገሩት የአካባቢው ነዋሪ፣ በችግር ሰዓት ሌባ እንደሚበዛና ሌላው በልቶ ሲያድር እየራበው ዝም ስለማይል ዝርፊያና ቅሚያ ይከሰታል የሚል ስጋት በህዝቡ ውስጥ እንዳለ አስረድተዋል፡፡ከፍተኛ የመንግስት አመራሮች ወደ አካባቢው በመጡ ጊዜ ያለውን ችግር እንደተመለከቱት የሚናገሩት የአካባቢው ነዋሪ፣ ህብረተሰቡ ከገዥው መንግስት እርዳታ እናገኛለን የሚል ተስፋ ቢኖረውም እስካሁን ምንም ዓይነት እርዳታ እንዳላገኘ ገልጸዋል።
በሰሜን ወሎ ዞን የሚገኙ አብዛኛው ወንዞች ምንም አይነት ውኃ በውስጣቸው የሌላቸው ከመሆኑ ባሻገር ትልልቅ የነበሩ ወንዞችም አነስተኛ የውሃ መጠን ብቻ መያዛቸውን የአካባቢው ነዋሪዎች ለኢሳት ገልጸዋል፡፡
በተመሳሳይ በዋግ ኽምራ ከሚገኙ ሰባት ወረዳዎች ውስጥ በደሃና እና ጋዝጊብላ ወረዳዎች ዘግይቶም ቢሆን ዝናብ የጀመረ ሲሆን፣ በሌሎች ወረዳዎች አጥጋቢ የሚባል ዝናብ ባለመኖሩ ህብረተሰቡ በመጪው ዓመት ሊቸገር እንደሚችል ነዋሪዎች ይናገራሉ፡፡
በሌላ በኩል የኢህአዴግ ባለስልጣናት ኢኮኖሚውን በተመለከተ በአደባባይ የሚናገሩት እና ለድርጅታቸው አባላት የሚናገሩት የተለያየ መሆኑን ከዚህ ቀደም የተለቀቁ በርካታ ማስረጃዎች መኖራቸው ቢታወቅም፣ የብአዴን ም/ል ሊቀመንበርና የአማራ ክልል ፕሬዚዳንት ገዱ አንዳርጋቸው በሰሞኑ የብአዴን ምክር ቤት ላይ ያቀረቡት አስተያየት፣ የገዢውን ፓርቲ የፕሮፓጋንዳ ባህሪ የሚያሳይ ሆኗል። አቶ ገዱ በግብርናውም ሆነ በእንዱስትሪው መስክ የረባ ውጤት አለመገኘቱን ይገልጻሉ። መልካም አስተዳደር የሚባለውም የባሰ ነው ይላሉ።
“አሁንም ድህነት ስር የሰደደ ችግር ነው፣ አሁንም የሚራብ ህዝብ አለ፣ በዝቅተኛ የአኗኗር ሁኔታ ውስጥ የሚኖር አለ፣ ከግብርና አኳያም፣ በቤተሰብ ደረጃም ሆነ በአካባቢ ደረጃ እርዳታ የሚፈልግ አለ” ሲሉ፣ የሚናገሩት አቶ ገዱ፣ አሁንም በዝቅተኛ ምርታማነት ደረጃ ላይ እንገናኛለን ይላሉ
እንዱስትሪው በእጅጉ ዝቅተኛ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ የሚገልጹት ባለስልጣኑ፣ ግንባታው ሲደመር ብቻ ነው የኢንዱስትሪ እድገቱን ከፍ ተብሎአል ተብሎ የሚነገረው ይላሉ
አቶ ገዱ መሰረተ ልማቱ ጥራት የለውም ይላሉ። “መብራት በቀን 12 ጊዜ ጠፋ ይባላል፣ 5 ጊዜ ጠፋ ቢባል ሰው ግር ሊለው ይችላል፣ በትክክል ግን በአንድ ቀን 12 ጊዜ መብራት በደብረማርቆስ ጠፍቷል። ይሄ በሁሉም ከተሞች በተመሳሳይ የሚታይ ችግር በመሆኑ፣ መብራት ሳይስተካከል ከተሞች ሊያድጉ አይቸሉም” ብለዋል ። መንግስት በይፋ ሳያውጅ ፣ ከሁለት እና ሶስት አመታት በላይ መብራት በፈረቃ የሚያገኙ ከተሞች መኖራቸውንም ባለስልጣኑ ገልጸዋል።