ታኅሣሥ ፲፱ (አሥራ ዘጠኝ)ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- ሰሞኑን በባህርዳር ከተማ በተካሄደው የጸረሙስና አውደጥናት ላይ እንደተገለጸው የአማራ ክልል ጸረሙስና ኮሚሽን ስራውን በአግባቡ ከመስራት ይልቅ በርካታ ሙሰኞችን ስራ በመደባበቅ ላይ መሆኑን ተሳታፊዎች አጋልጠዋል፡፡
“ለልማት፣ ለሰላምና ለደህንነት በሙስና ላይ የተባበረ ክንድን ማንሳት!!” በሚል መሪ ቃል ለ12ኛ ጊዜ በሚከበረው የጸረሙስና ቀን ጥናት አቅራቢው እንደተናገሩት በአማራ ክልል ከሚገኙ መንግስታዊ መስሪያቤቶች ውስጥ በፌደራል ደረጃ ከፍተኛ ምዝበራ ይካሄድባቸዋል ተብለው ከተፈረጁት መካከል የአማራ ውሃ ስራዎች ይገኝበታል።
ድርጅቱ በፌደራል ጸረሙስና ኮሚሽን በብልሹ አሰራሩ ከተፈረጁት መካከል አንዱ ቢሆንም የክልሉ ጸረሙስና ኮሚሽን ግን ሃላፊነቱን በመውሰድ ድርጅቱን ሊታደግ አለመቻሉ በሰራተኛው ዘንድ ጥያቄ እንደፈጠረ የድርጅቱ ስነምግባር መኮንን ተናግረዋል፡፡
የድርጅቱ ሰራተኞች በጸረሙስና ኮሚሽኑ እምነት በማጣት ከሰራተኛው የተወጣጡ “የሙስና አጣሪ አብይ ኮሚቴ ” በማቋቋም በድርጅቱ አመራሮችና ሰራተኞች የተሰሩትን የሙስና ወንጀሎች ለስድስት ወር በማጥናት ውጤታማ ስራ መሰራቱን መኮንኑ ተናግረዋል፡፡ ከሰራተኛው የተወጣጣው “የሙስና አጣሪ አብይ ኮሚቴ ” ያገኛቸውን ጉድለቶች በማጋለጥ ከተሟላ ማስረጃ ጋር ለክልሉ ርዕሰ መስተዳደር ጽህፈት ቤት፣ለጸረ ሙስና ኮሚሽን፣ ለክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን፣ለድርጅቱ ቦርድ እና ማኔጅመንት አመራር አካላት እንዳቀረቡ የተናገሩት የድርጅቱ ስነምግባር መኮንን መረጃው ከደረሳቸው አመራሮች መካከል ጉዳዩን ትኩረት ሰጥቶ በመንቀሳቀስ ለማጣራት የሞከረም ሆነ ርምጃ የወሰደ ባለመኖሩ መላው የድርጅቱ ሰራተኞች ግራ መጋባታቸውን ተናግረዋል፡፡
ሙስና ሰሩ በሚል በሰራተኞች የተጋለጡና በማስረጃ የተረጋገጠባቸውን የስራ ኃላፊዎች ዘግይቶም ቢሆን የደመዎዝ ቅነሳም ሆነ ሌላ ምንም ዓይነት አስተማሪ እርምጃ ሳይወሰድ ከአንድ ክፍል ወደ ሌላ ክፍል በማዛወር የሰሩትን ስራ ለማዳፈን ከመሞከር ውጭ የሰራተኛውን ጥያቄ የሚያረካ ምላሽ አለመሰጠቱን የተናገሩት መኮንን የጸረሙስና ኮሚሽኑ በቀረበለት ሪፖርትና ማስረጃ መሰረት መውሰድ የሚገባውን እርምጃ አለመውሰዱ ስራውን በአግባቡ እየተወጣ እንዳልሆነ ማሳያ መሆኑን ይናገራሉ፡፡
“ኮሚሽኑ ስራውን አቁሟል፣ ቀዝቅዟል” የሚሉት የስነምግባር መኮንን በድርጅቱ ውስጥ ተጀምሮ የቀረው የሃብት ማስመዝገብ ሂደቱን ባላከናወኑ ሃላፊዎች ላይም የተወሰደ እርምጃ አለመኖሩ የድርጅቱ ሰራተኞች በኮሚሽኑ አሰራር ላይ ጥርጣሬያቸው ከፍ እንዲልና ተስፋ እንዲቆርጡ ማድረጉን ተናግረዋል።