የሙስሊሞች የመፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴ አባላት ጉዳይ ለጥቅምት ተቀጠረ

(Sept. 14) በአስር ላይ የሚገኙት፤ የሙስሊሞች የመፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴ አባላት ጉዳይ፤ ለመጪው ጥቅምት 1 ቀን መቀጠሩን፤ የአዲስ አበባ ምንጮቻችን ገለጹ።
በቀጠሯቸው መሰረት ከ28 ቀን በሁዋላ ትናንትና ሀሙስ መስከረም ሶስት ቀን በማረሚያ ቤት ሰራተኞች ወደፍርድ ቤት መቅረብ ያልቻሉት ተከሳሾች፤ ዛሬ አርብ በከፍጠኛ ጥበቃ ፍ/ቤት እንደቀረቡ ታውቋል።
በዛሬው ችሎትም፤ አቃቤ ሕግ ምርመራዬን አልጨረስኩም ብሎ በጠየቀው መሰረት፤ ፍ/ቤቴ ለአቃቤ ሕግ ተጨማሪ 28 ቀን ፈቅዶለት፤ እስረኞቹ ለመጪው ጥቅምት 1 መቀጠራቸው ታውቋል።
የትናንትናውም የዛሬውም ችሎት ለህዝብ ዝግ የነበረ ቢሆንም፤ ከፍ/ቤቱ ውጪ በሺሆች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያዊያን ተገኝተው ለእስረኞቹ ያላቸውን አጋርነት እንዳሳዩ ተገልጿል።
በስፍራው የተገኙ የእስልምና እምነት ተከታዮችም በአራዳ ፍ/ቤት ዙሪያና በአጼ ምኒሊክ ሀውልት ግቢ ውስጥ ጸሎታቸውንና ስግደታቸውን እንዳደረጉም ከስፍራው የደረሰን መረጃ ያመለክታል።
የመፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴዎቹ የታሰሩት ባለፈው ሀምሌ አጋማሽ ሲሆን፤ አቃቤ ህግ ቀጠሮ ሲጠይቅባቸውና ፍ/ቤቱ የአቃቤ ህግን ጥያቄ ያለምንም ምርመራ ሲፈቅድ ለሁለተኛ ግዜ መሆኑ ታውቋል።
እስረኞቹ የአቶ መለስን ሞት ተከትሎ በነበረው ብሄራዊ የሀዘን ወቅት ከፍተኛ ሰቆቃና ድብደባ እንደተፈጸመባቸው ቤተሰቦቻቸው የተናገሩ ሲሆን፤ አንዳንዶቹ ከድብደባው ብዛት የተነሳ ሰውነታቸው እንዳባበጠና መቆምና መራመድ እንተሳናቸውም ታውቋል።
እስረኞቹ ከታሰሩ ወደ ሁለት ወር ቢጠጋቸውም፤ እስካሁን ክስ እንዳተመሰረተባቸው ወይም የተከሰሱበት ወንጀል ዝርዝር እንዳልደረሳቸው የታወቀ ሲሆን፤ በተጨማሪም ከቅርብ ግዜ ወዲህ ከጠበቆቻቸው ጋር መገናኘት እንዳልቻሉም ታውቋል።
በተያያዘ ዜና በሙስሊሞች ላይ የሚደርሰው ሰቆቃና ድብደባ በተለያዩ የውጭ ከተሞች ከፍተኛ ተቃውሞን እየቀሰቀሰ ሲሆን፤ በዛሬው እለት በጄኔቭ ስዊትዘርላንድ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን፤ በተባበሩት መንግስታት የሰብአዊ መብት ኮሚሽን ጽ/ቤት ፊት ለፊት ከፍተኛ የተቃውሞ ሰልፍ እያደረጉ እንደሆን ከስፍራው የደረሰን ዜና ያስረዳል።