የሙስሊም መፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴ አባላት ፍርድ ቤት ቀረቡ

ጥር ፳፯ (ሃያ ሰባት) ቀን ፳፻፮ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-የታሳሪ ቤተሰቦች፣ የሚዲያ ባለሞያዎችና የውጭ አገራት ዲፕሎማቶች  በተገኙበት በተካሄደው ችሎት  የታሳሪ ጠበቆች የምስክሮቻቸውን አድራሻ አሟልተው አለማቅረባቸው በፍርድ ቤቱ ተገልጿል።

ጠበቆቹ የምስክሮችን ስም በፍጥነት ለማስታወቅ ያልቻሉት ጂሃዳዊ ሐረካት ፊልም ለህዝብ መለቀቁን ተከትሎ በምስክሮች ላይ ፍርሀት በማደሩና የተለያዩ አካላት ስለሚያስፈራሯቸው ለደህንነታቸው በመስጋታቸው መሆኑን እንዲሁም የሰነድና የቪዲዮ ማስረጃዎች ለማቅረብ ደግሞ ተጨማሪ ጊዜ የሚያስፈልግ መሆኑን በመግለጽ ተከራክረዋል።

አቃቤ ህግ የጠበቆችን ንግግር ተቃውሞአል። ጠበቆቹ የወሰዱት ጊዜ በቂ በመሆኑ ማስረጃዎችን አጠናክረው እንዲያቀርቡም ጠይቋል።

የሙስሊሙ መፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴ ሰብሳቢ ኡስታዝ አቡበከር አህመድ በበኩላቸው በሺዎች የሚቆጠሩ ምስክሮችን አዘጋጅተው የነበረ ቢሆንም በተደጋጋሚ ከፖሊስና ከደህንነት በሚደርስባቸው ማስፈራሪያ ሳቢያ ‹‹የሚደርስብንን ችግር ተቋቁመን ለመመስከር ዝግጁ ነን›› ያሉትን ስም ዝርዝር ብቻ ማስገባታቸውን፣ የእነዚሁ መስካሪዎች አድራሻ ያልተጠቀሰውም ከደህንነት ስጋት እንደሆነ በመግለጽ ለማስረዳት ሞክረዋል።

ዳኛው በበለኩላቸው የምስክሮች ስምና አድራሻ፣ የሚመሰክሩለት ግለሰብና የሚመሰክሩት ጭብጥ በሙሉ ተሟልቶ መቅረብ እንዳለበት አሳስበዋል፡፡

አቶ አህመዲን ጀበል በበኩላቸው ታሳሪዎች ችሎት ፊት የቀረቡት ለታሪክ ምስክርነት እንጂ ፍትህን ጠብቀው እንዳልሆነ ገልጸው ‹‹የአቃቤ ህግ ምስክሮችን ደህንነት ለመጠበቅ›› በሚል ፍርድ ቤቱ ሲፈቅድ የነበራቸውን አሰራሮች በመጥቀስና በማነጻጸር ችሎቱን በመስቀለኛ ጥያቄ አፋጠዋል፡፡

‹‹የአቃቤ ህግ ምስክሮች የፖሊስም፣ የወታደርም የመንግስትም ድጋፍ እየተደረገላቸው እንኳ ደህንነታቸውን ለመጠበቅ በሚል ስም ዝርዝርና አድራሻቸው ሳይደርሳቸው ምስክርነታቸው እንዲሰማ ተፈቅዶ ሳለ፣ የተከሳሽ ምስክሮች ግን የግድ አድራሻቸው መታወቅ አለበት ተብሎ መነገሩ ትክክል አይደለም በማለት ተከራክረዋል።

ኡስታዝ አቡበክር ተጨማሪ ነገሮችን ለመናገር ሲጀምሩ  የጥበቃ ሐላፊው ያለዳኞቹ ትእዛዝ አስቁመውታል፡፡

ዳኞች በመጨረሻም የታሳሪ ጠበቆች የምስክሮች ስምና አድራሻ፣ የሚመሰክሩለትን ግለሰብና የሚመሰክሩበትን ጭብጥ በሙሉ አሟልተው ከሰነድና ቪዲዮ ማስረጃዎች ጭምር ለመጋቢት 16 እንዲያቀርቡና ለ15 ቀናት ያህልም ለችሎቱ እንዲያሰሙ ውሳኔ በመስጠት ችሎቱን አሰናብተዋል፡፡

የመፍትሄ አፈላላጊ አባላት ምንም አይነት የመንፈስ መረበሽ እንዳልታየባቸው በስፍራው የነበሩ ታዛቢዎች ገልጸዋል።