መጋቢት ፲ (አስር) ቀን ፳፻፬ ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጽ/ቤት (መጅሊስ) ሕዝበ ሙስሊሙ እያካሄደ ያለውን ሠላማዊ ትግል ሊያጨናግፍ የሚችል አቻ ኮሚቴዎችን አዋቅሮ የግብረ ኃይል የሥራ ተዋረድ እንደሰጣቸውና የመንግሥት ተወካዮች በእጅ አዙር ድጋፋቸውን እንደገለጹለት የመጅሊስ ምንጮቻችን አስታወቁ፡፡
ቅዳሜ መጋቢት 8 ቀን 2004 ዓ.ም ጦር ኃይሎች አካባቢ ከሆላንድ ኤንባሲ አቅራቢያ በሚገኘው የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጽ/ቤት (መጅሊስ) ቅጥር ጊቢ ከሁለት ሺህ ያላነሱ የየመስኪዶቹን የመጅሊስ ተወካዮቹንና የኢህአዴግ ካድሬ ደጋፊዎቹን ለግማሽ ቀን ያህል ካወያየ በኋላ ነበር ግብረ ኃይሉ የተቋቋመው፡፡
እንደ ምንጮቻችን ገለጻ ወደ የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጽ/ቤት ቅጽር ጊቢ ተጋባዦች ሲገቡ በርካታ የየመስኪዱ የመጅሊስ ተወካዮች በር ላይ ቆመው የጥሪ ወረቀት መያዛቸውንና ሰዎቹ በየቀኑ የሚታደሙበትን መስኪድ እየገለጹ በየመስኪዱ ወኪሎቻቸው በኩል የይግባ አይግባ ይለፍ ውሳኔ ሲተላለፍ ተስተውሏል፡፡
የመንግሥት ተሻሚዎች ናቸው ተብለው በሕዝብ ሙስሊሙ የሚብጠለጠሉ የመጅሊስ ከፍተኛ አመራሮች ከየመስኪዱ ደጋፊ ኢማሞች ጋር ባደረገው ውይይት ይሄን ተገቢ ያልሆነ የ“ዋህቢዮች” ሕዝባዊ ተቃውሞ ለመበተን የሚያስችል የግብረ ኃይል እንቅስቃሴው ተጠናክሮ ይቀጥላል፤ የመንግሥት ክትትልና ድጋፍም አይለየውም ብለዋል፡፡
አንዳንድ ተሳታፊ የሆኑ የሃይማኖቱ ኢማሞች፣ ዱዓቶች (ዳዒ) እና ኢማሞች ይሄ ነገር ለሕይወታችንም ያሰጋናል በማለታቸው ከአመራሮቹ ይህ እንዳይሆን የመንግሥት የደህንነት ሠራተኞች ከጎናችን አሉ አትፍሩ ብለዋል ሲሉ ምንጮቻችን አስረድተዋል፡፡
በስብሰባው ማጠቃለያ ላይ የአሕባሽ መሥራች እንደሆነ የሚነገርለት የሸህ አብደላ አል ሀረሪ መጽሐፍቶች ለታዳሚያኑ መበተኑን ዘጋቢያችን ከተሳታፊዎቹ አረጋግጧል ፡፡
በዚህ ስብሰባ ላይ በርካታ የመስኪድ ዳዒዎች፣ ዑስታሶች፣ ኢማሞች እና ዑላማዎች የአወሊያ መጅሊስ አይወክለንም ፣ ይውረድ እንቅስቃሴ ደጋፊ ናቸው ተብለው ወደ መጅሊስ ቅጥር ጊቢ እንዳይገቡ መከልከላቸውን ለማወቅ ተችሏል፡፡
___________________________________________________________________________________________________________________________________________________________________________
ESAT is the first independent Ethiopian satellite service tasked to produce accurate and balanced news and information, as well as other entertainment, sports and cultural programming created for and by Ethiopians.
ESAT is committed to the highest standards of broadcast journalism and programming and will strive to provide an outlet of expression to all segments of the diverse Ethiopian community worldwide