የመጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት በመጓዝ ላይ የሚገኙ እስረኞች ለማምለጥ ባደረጉት ሙከራ በፖሊስ ጥይት ተገደሉ

ጥቅምት ፲፮ (አስራ ስድስት) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-በአ/አ በተለምዶ ጦር ኃይሎች ቶታል እየተባለ በሚጠራ አካባቢ ወደሚገኝ የፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት በመጓዝ
ላይ የሚገኙ እስረኞች ለማምለጥ ባደረጉት ሙከራ በፖሊስ ጥይት ተገደሉ፡፡ ሁለት እስረኞች በጥይት ተመተው
ሞተዋል፡፡
ፖሊስ ዛሬ ከቀኑ 7፡00 ሰዓት ገደማ እስረኞቹን ፍ/ቤት ለማቅረብ በጉዞ ላይ እንደነበረና ፍ/ቤቱ አካባቢ
ሲደርሱ ግን በርበሬ መሰል ነገር ፖሊሶቹ ዓይን ላይ በመበተን ለማምለጥ ሙከራ አድርገዋል፡፡

ለማምለጥ ከሞከሩት መካከል ሁለቱ ወዲያውኑ በፖሊሶች ጥይት በቅርብ ርቀት ተመትተው መገደላቸውን የዓይን እማኞቹ አረጋግጠዋል፡፡በዚህ የእስረኞች የማምለጥ ሙከራ ለጊዜው የተሳካላቸው መኖራቸውን እማኞቹ ገልጸው ቁጥራቸው ግን ምንያህል እንደሆነ ለማወቅ አለመቻላቸውን ተናግረዋል፡፡

የማምለጥ ሙከራውን ተከትሎ ፖሊሶች አካባቢውን በተኩስ እሩምታ ማመሳቸውን እማኞቹ ጠቁመው በመንገድ ጉዞ ላይ ከነበሩ በርካታ ተሸከርካሪዎች መካከል በአንዲት ሴት ሲሽከረከር የነበረ የቤት መኪና አካል ላይ ጉዳት ደርሶ ማየታቸውን እማኞቹ ጠቅሰዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት በአ/አ ከሚገኙ የፌዴራል ማረሚያ ቤቶች ታራሚዎች መካከል 62 በመቶ በአእምሮ ሕመምና ጭንቀት
ችግር የተጠቁ መሆናቸውን በአገር ቤት የሚታተም አንድ ጋዜጣ የጤና ጥበቃ ሚኒስቴርን ምንጭ ጠቅሶ ሰሞኑን መዘገቡ
ይታወሳል””