ኢሳት (ሰኔ 19 ፥ 2009)
የሳውዲ አረቢያ መንግስት ህጋዊ የመኖሪያ ፈቃድ የሌላቸውን የውጪ ሐገር ዜጎች ሀገር ለቀው አንዲወጡ ያስቀመጠው ቀነ ገደብ ቢጠናቀቅም ከመቶ ሺዎች በላይ ኢትዮጵያዊያን ከሳውዲ አንዳልወጡ ህወሐት መራሹ መንግስት አመነ ። የጉዞ ሰነድ ከወሰዱት ወደ አገር ቤት የተመለሱት ከ 42 በመቶ በታች ነው።
የሳውዲ ኣረቢያ መንግስት ከመጋቢት 21 ቀን 2009 አ/ም ጀምሮ በነበሩበት ተከታታይ ሶስት ወራት ሕጋዊ የመኖሪያ ፍቃድ የሌላቸው የማንኛውም ሀገር ዜጎች ሀገሪቱን ለቀው አንዲወጡ የሰጠው ቀነ ገደብ ያበቃው ቅዳሜ ሰኔ 17 ቀን 2009 ቢሆንም ወደ ኢትዮጵያ የተመለሱ ኣነስተኛ መሆናቸውን የመንግስት ቃል ኣቀባይ ዶ/ር ነገሪ ሌንጮ ገልጸዋል።
የ 2009 አ/ም የበጀት አመት ማጠቃለያን አስመልክተው ለመንግስት፣ ለገዢው ፓርቲ ሚዲያዎችና ለአገዛዙ ቅርበት ላላቸው የሀገር ውስጥ ፕሬሶች መግለጫ የሰጡት ዶ/ር ነገሪ ሌንጮ እንደገለጹት ከሆነ አስካለፈው ሳምንት መጨረሻ ድረስ ሳውዲን ለቀው ወደ ኢትዮጵያ ለመመለስ የጉዞ ሰነድ የወሰዱት ዜጎች 85 ሺ ያህል ብቻ ናቸው። ቃል- አቀባዩ አያይዘው እንደገለጹት የጉዞ ሰነድ ከወሰዱት 85 ሺህ ያህሉ ወደ አገር ቤት መመለስ የቻሉት 35 ሺ ብቻ መሆናቸውን ገልጸዋል። ይህ ቁጥር በሳውዲ ኣረቢያ ይኖራሉ ተብለው ከሚገመቱ ህጋዊ መኖሪያ ፍቃድ የሌላቸው በመቶ ሺዎች ኢትዮጵያውያን ጋር ሲነጻጸር አጅግ አነስተኛ መሆኑን በሳውዲ የሚገኙ የኢሳት ምንጮች ተናግረዋል።
ከሳውዲ የመውጫ ቀነ-ገደቡ መጠናቀቁ እየታወቀ ሌሎች የትራንስፖርት አማራጮችን ለመጠቀም አቅደናል በማለት ቃል አቀባዩ መግለጻቸውን ከተጠያቂነት ለመሸሽ እንደሆነ የሚገልጹት በሳውዲ የሚገኙ የኢሳት ምንጮች ኢትዮጵያውያን ከሳውዲ በመውጣት ወደ ጎረቤት ሀገሮች በመሸሽ ላይ እንደሚገኙ ተናግረዋል። በተለይም መንግስት አልባ ወደ ሆነችው የመን የሚሸሹት ኢትዮጵያዊያን ቁጥራቸው እየጨመረ መሄዱ አሳሳቢ እየሆነ መሄዱንና ተጨማሪ ስቃይና አንግልት የምንሰማበት ጊዜ እንዳይመጣ ሲሉ ስጋታቸውን ገልጸዋል።