(ኢሳት ዲሲ–መስከረም 30/2011) በአዲስ አበባ ወደ ቤተ መንግስት በማምራት የደሞዝ ጭማሪና ጥቅማጥቅም ያነሱ የመከላከያ ሰራዊት አባላት ከጠቅላይ ሚንስትር አብይ አህመድ ጋር መወያየታቸውን የፌዴራል ፖሊስ ጄኔራል ኮሚሽነር አቶ ዘይኑ ጀማል ገለጹ።
ወታደሮቹ ከሃዋሳ መጥተው ለጸጥታ ጥበቃ በቡራዩ ተልእኮ ላይ የነበሩ የሰራዊት አባላት መሆናቸውንም ኮሚሽነሩ ከአሜሪካ ድምጽ ጋር ባደረጉት ቃለምልልስ ገልጸዋል።
በቁጥር 250 የሚደርሱት የመከላከያ ሰራዊት አባላት ከነጠበንጃቸው ወደ ቤተመንግስት በማምራት ጠቅላይ ሚንስትር አብይ አሕመድ እንዲያነጋግሯቸው ጠይቀዋል።
ኮሚሽነር ዘይኑ ጀማል እንዳሉት ወታደሮቹ ከነጠበንጃቸው ቤተመንግስት መግባት ፈልገው ተከልክለዋል።
በዚህም ምክንያት በቤተመንግስት አካባቢ ግርግር ተፈጥሮ እንደነበር ኮሚሽነሩ ገልጸዋል።
በመጨረሻም ወታደሮቹ ከጠቅላይ ሚንስትር ዶክተር አብይ አህመድና ምኽጥል ጠቀላይ ሚንስትር ደመቀ መኮንን ጋር ተወያየተው ችግሩ በሰላም ተፈቷል ብለዋል።
የደሞወዝና የጥቀማጥቅም ጠያቄ ያነሱት ወታደሮች ጠቅላይ ሚንስትር አህመድን የምንወዳቸው መሪ ናቸው፥ማነገር የምንፈልገውም እርሳቸውን ብቻ ነው ብለው እንደነበርም ተገልጿል።
የወታደሮቹ ጥያቄን ተከትሎ በቤተ መንግስት አካባቢ ከፍተኛ ጠበቃ እየተደረገ መሆኑን የኢሳት ምንጮች አረጋግጠዋል።