የመከላከያ ሰራዊት አባላት በህዝቡ ላይ የሚወስዱትን እርምጃ ነዋሪዎች በሰልፍ ተቃወሙ

ጥቅምት ፲(አስር) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-በምእራብ አርማጭሆ የመከላከያ ሰራዊትን የሚከዱ ወታደሮችን ቁጥር እየጨመረ በመምጣቱ፣ በአካባቢው የሚገኙት ወታደሮች በህዝቡ ላይ የአጸፋ እርምጃ እየወሰዱ ነው። የምእራብ አርማጭሆ ወረዳ ነዋሪዎች እሁድ እለት የተቃውሞ ሰልፍ ያደረጉ ሲሆን፣ ለአሁኑ ሰልፍ ምክንያት የሆነው ጥቅምት 7 አንድ ወታደር መጥፋቱን ተከትሎ የአጎቱ ልጅ የሆነ የጤና ባለሙያ ከፍተኛ ድብደባ ደርሶበት እንዲታሰር ከተደረገ በሁዋላ ነው።

በቅርቡ አንድ የሚሊሻ አባል ጠመንጃ መጥፋቱን ተከትሎ ማሩ ወይም በተለምዶ ቄሴ የተባለ ሰው ተይዞ ሰውነቱ ጉድጓድ ውስጥ ተቀብሮ በበርበሬ እንዲታጠንና እንዲደበደብ ከተደረገ በሁዋላ ለአካል ጉዳት የተዳረገ ሲሆን፣ ከዚሁ ጋር በተያያዘ አየነው አለሙ የሚባሉና ሌሎችም ሰዎች ታስረው ከፍተኛ እንግልት ደርሶባቸዋል።

ነዋሪዎች እንደሚሉት ጥቅምት 7 ቀን የጠፋውን ወታደር ተከትሎ አጎቱ ነው የተባለው የጤና ባለሙያ እንዲያዝ ከተደረገ በሁዋላ ከፍተኛ ድብደባ ሲካሄድበት በማደሩ ለአካል ጉዳት ተደርጓል። የጤና ባለሙያው የደረሰበትን ከፍተኛ ጉዳት ተከትሎ 200 የሚሆኑ የከተማዋ ነዋሪዎች ወደ አስተዳደሩ በመሄድ ጥያቄ ያቀረቡ ሲሆን የወረዳው አስተዳዳሪ  ጉዳዩ የመከላከያ በመሆኑ እንደማያገባቸው በመግለጻቸው ውዝግብ ተፈጥሮ ነበር።

የወረዳዋ የጤና ባለሙያዎች በበኩላቸው ባልደረባችን ካልተፈታ ስራ አንሰራም በማለት ለግማሽ ቀን ስራ አቁመው ውለዋል። ከወታደሩ መጥፋት ጋር በተያያዘ ሴቶችና ወንዶችም ተይዘው እየተደበደቡ ነው።

ያነጋገርናቸው ነዋሪዎች እንደሚሉት በአካባቢያቸው የሰፈረውን  የመከላከያ ሰራዊት እየተው የሚጠፉ ብዙ ናቸው። ወታደሮቹ በጠፉ ቁጥር በነዋሪው ላይ የሚደርሰው እንግልትም በዚያው ልክ ይጨምራል።