የመከላከያ ሰራዊት አባላት ምህረት ተደረገላቸው

(ኢሳት ዲሲ–ሐምሌ 26/2010)በወታደራዊ ልዩ ልዩ  ወንጀሎች ለተከሰሱ የመከላከያ ሰራዊት አባላት ምህረት ማድረጉን የመከላከያ ሚኒስቴር አስታወቀ።

ለመከላከያ ሰራዊት አባላቱ ምህረት የተደረገው በቅርቡ ያጸደቀውን የምህረት አዋጅ መሰረት በማድረግ ነው ተብሏል።

በወታደራዊ የስነ ምግባር ጥሰት ተከሰው በማረሚያ ቤት የሚገኙና ቀደም ሲል ከሃገር የኮበለሉ የሰራዊት አባላት ምህረት እንደተደረገላቸው ታውቋል።

የምህረት አዋጁ የሚመለከታቸው የሰራዊት አባላት ተቋሙ ባዘጋጃቸው አካባቢዎች ባሉ ጽህፈት ቤቶች በአካልም ሆነ በተዘጋጀ ፎርም ማመልከት እንደሚገባቸውም ነው የተገለጸው።

በዚህም በተቋሙ አዲስ አበባና አካባቢዋ የሚገኙ ታራሚዎች ቤላ አካባቢ በሚገኘው የፍትህ ዳይሬክቶሬት ጽህፈት ቤት ሪፖርት ማድረግ እንደሚችሉ ተነግሯል።

ከአዲስ አበባ ውጭ ላሉ ታራሚዎች ባሉበት ክልል በተጠባባቂ የፍትህ ዳይሬክቶሬት ጽህፈት ቤት ሪፖርት ማድረግ ይችላሉ ተብሏል።

በወረዳና በዞን ላሉ ደግሞ በዞኑ በሚገኘው ጽህፈት ቤት ሪፖርት ማድረግ ይጠበቅባቸዋል።

ዘገባዎቹ እንዳመለከቱት ጽህፈት ቤቱ ፎርሙን ማስሞላት መጀመሩም ታውቋል።

በክልሎች ደግሞ ከነሃሴ አንድ ቀን ጀምሮ ባሉት ስድስት ወራት ውስጥ ሪፖርት ማድረግ ይቻላል ተብሏል።

በተሰጠው የጊዜ ገደብ ውስጥ ሪፖርት አድርገው ያላጠናቀቁ ታራሚዎች የጊዜ ገደቡ ሲጠናቀቅ ሪፖርታቸው ተቀባይነት እንደማይኖረውም የመከላከያ ሚኒስቴር አስታወቋል።