የመከላከያ መሃንዲሶችና  መምህሮቻቸው ወደ ጦር ግንባር እንዲዘምቱ መደረጉን ተቃወሙ

ሰኔ (አሥራ  አምስት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- በሜ/ጄኔራል ሙሉጌታ ቡሊ ቴክኒክ ኮሌጅና በደብረዘይት ወታደራዊ ምህንድስ ክፍል ውስጥ  ሲሰሩ የነበሩ በርካታ ወታደራዊ መሃንዲሶች፣ የጥገና ሰራተኞች እና መምህራን የኢትዮ-ኤርትራ ግጭት ከመነሳቱ ከ2 ሳምንት በፊት ወደ ኢትዮ-ኤርትራ ድንበር መላካቸውን የኢሳት ምንጮች ገልጸዋል።

ሰራተኞቹ “ከዚህ ቀደም ተደርጎ የማያውቅ ነው” በማለት ወደ ግንባር መላካቸውን ቢቃወሙም፣ የሚሰማቸው አለማግኘታቸውን ገልጸዋል። ከሁለቱ ወታደራዊ ማሰልጠኛዎች ብቻ ከ30 በላይ የምህንድስና አስተማሪዎች ወደ ግንባር የተላኩ ሲሆን፣ ሁሉም በብሄራችን የተነሳ ተመርጠን ወደ ግንባር እንድንላክ ተደርጓል በማለት ቅሬታ ያሰማሉ። ኢሳት የተላኩት መምህራን ስም ዝርዝር ያለው ሲሆን ለደህንነታቸው በመስጋት ይፋ አያደርግም።

ምንጮቻችን እንደገለጹት ከተለያዩ ወታደራዊ ክፍሎች እየተመረጡ ወደ ግንባር የተላኩት ቁጥራቸው በመቶዎች ይደርሳል።

ወታደራዊ መሃንዲሶቹ ከግጭቱ በፊት ወደ ግንባር መላካቸው የኢህአዴግ መንግስት አስቀድሞ ለጦርነት ሲዘጋጅ እንደነበር ማሳያ ነው የሚሉት ምንጮች፣ ከግጭቱ በሁዋላም ቢሆን በአካባቢው ከፍተኛ ወታደራዊ እንቅስቃሴ እንዳለ ይገልጻሉ።

ወደ ግንባር የተላኩት አብዛኞቹ ሰራተኞች መንግስትን የሚቃወሙና አጋጣሚውን ተጠቅመው ተቃዋሚዎችን ለመቀላቀል ፍላጎት ያላቸው መሆኑን ምንጮች አክለው ተናግረዋል።

ከዚሁ ጋር በተያያዘ ኢትዮጵያ ሙሉ ጦርነት ለማድረግ በዝግጅት ላይ መሆኑዋን በኤርትራ የፕሬዚዳንቱ አማካሪ የማነ ገብረአብ ጄኔቭ ለሚገኘው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብአዊ መብት ኮሚሽን ተናግረዋል።

አቶ የማነ “ እዚህ በምንነጋገርበት ወቅት ኢትዮጵያ በኤርትራ ላይ ሙሉ ጦርነት ለመክፈት ዝግጅት እያደረገች ነው “ ብለዋል።

፣ የተመድ የሰብአዊ መብት ድርጅት በኤርትራ ላይ ያቀረበው ሪፖርት ኢትዮጵያ በኤርትራ  ላይ ጦርነት ለመክፈት ከመቼውም ጊዜ በላይ ጥሩ አጋጣሚ እንደፈጠረላት ታምናለች ያሉት አቶ የማነ፣ ሪፖርቱ በዜጓቸ ላይ ለምትፈጽመው ወንጀልም ሆነ በኤርትራ ላይ ለመፈጸም ላሰበችው ጥቃት ጥሩ ምክንያት እንደፈጠረላት አክለዋል።

ኢትዮጵያ በኤርትራ ላይ ጥቃት ለመሰንዘር አስባለች ብለው እንዲናገሩ ያደረገቻውን ምክንያት የተጠየቁት አቶ የማነ፣ “ እነሱ ራሳቸው ለረጅም ጊዜ ሲሉት የነበረ ነገር ነው፤ እኛም በድንበር አካባቢ ሃይላቸውን ሲያጠናክሩ እያየን ነው” የሚል መልስ ሰጥተዋል። ኤርትራ ራሱዋን ለመከላከል መዘጋጀቱዋንም አቶ የማነ አክለዋል።

ኤርትራ  በሰሞኑ ግጭት 18 ወታደሮቿ እንደተገደሉባት እና ለጸጥታው ምክርቤትም አቤት ማለቱዋን የኤርትራው ከፍተኛ ባለስልጣን ገልጸዋል።  በኢትዮጵያ በኩል 300 ወታደሮች መገደላቸውን ኤርትራ ማስታወቁዋ የሚታወስ ሲሆን፣ የኢህአዴግ መንግስት በኢትዮጵያ በኩል ስለደረሰው ጉዳትም ሆነ በኤርትራ ላይ ስለደረሰው ጉዳት ዝርዝር ማብራሪያ አልሰጠም። ኤርትራ የተገደሉ ወታደሮቿን በክብር መቅበሯ ታውቋል።

በሌላ በኩል አየር መንገድ ድሬዳዋ የነበረውን የበረራ ማሰልጠኛውን በአስቸኳይ በማንሳት ወደ መቀሌ እንዲዛወር በአየር ሃይል ከታዘዘ በሁዋላ ዛሬ 1ኛውን ሴሲና አውሮፕላን ወደ መቀሌ አዛውሯል። በአሁኑ ሰአት 4 Diamond Pilot Training Aircraft አውሮፕላኖች ድሬዳዋ የቀሩ ሲሆን እስከሚቀጥለው ሳምንት ወደ መቀሌ ይሄዳሉ ተብሎ ይጠበቃል።