ኢሳት (ሰኔ 27 ፥ 2008)
ሰሞኑን በአዲስ አበባ ላፍቶ ክፍለከተማ ዙሪያ “ህገወጥ” የተባሉ የመኖሪያ ቤቶችን ለማፍረስ ተካሄዶ በነበረው ዘመቻ ጋር በተገናኘ ከ200 በላይ ነዋሪዎች ለእስር ተዳረጉ።
የመኖሪያ ቤታቸው ያለምንም ቅድመ ሁኔታ በመፍረስ ላይ እንደሚገኝ የተናገሩት የአካባቢው ነዋሪዎች የጸጥታ ሃይሎች በጅምላ የእስራትና ድብደባ ድርጊት ሲፈጽሙ መሰንበታቸው ለመገናኛ ብዙሃን አስረድተዋል።
የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን የቤት ማፍረሱን ድርጊት ለማስተባበር በተሰማራበት በዚሁ ዘመቻ ባለፉት ስድስት ቀናት ብቻ ከ200 የሚበልጡ ነዋሪዎች ለእስር መዳረጋቸውንና በርካታ ሰዎች ድብደባ እንደተፈጸመባቸው አስታውቀዋል።
የጸጥታ ሃይሎች ሁለት የፖሊስ አባላትንና አንድ የወረዳ ስራ አስፈጻሚን ገድለዋል የተባሉ ተጠርጣሪዎችን በመያዝ እየወሰዱ ባለው ዘመቻ ከጉዳዩ ጋር ግንኙነት የሌላቸው ንጹሃን ሰዎች እንግልት እየደረሰባቸው መሆኑን ነዋሪዎች ዋቢ በማድረግ በሃገር ውስጥ የሚገኙ ጋዜጦች ዘግበዋል።
የአዲስ አበባ አስተዳደር በበኩሉ በአካባቢው ተገንብተው ከሚገኙ ከ30 ሺ በላይ የመኖሪያ ቤቶች መካከል አብዛኞቹ ህገወጥ መሆናቸው አስታውቆ ቤቶቹን የማፍረሱ ዜመቻ ተጠናክሮ መቀጠሉን ገልጿል።
ነዋሪዎቹ በበኩላቸው የከተማው አስተዳደር በቂ የማስጠንቀቂያ ጊዜን ሳይሰጥ ሰዎች በመኖሪያ ቤታቸው በሌሉ ጊዜ ቤቶችን ማፍረሱ ተገቢ አለመሆኑን ተናግረዋል።
የመኖሪያ ቤታቸውን ለመገንባትና ቦታን ለመግዛት በብዙ ሺህ የሚቆጠር ገንዘብ እንዳወጡ የሚገልጹት ነዋሪዎች፣ በመኖሪያ ስፍራ መፍረስ ተደራራቢ ችግሮች እንደደረሱባቸው አስረድተዋል።
ለቀናት ዘልቆ በነበረው በዚሁ ግጭት እስካሁን ድረስ ስድስት ሰዎች የተገደሉ ሲሆን፣ ሁለቱ የፖሊስ አባላት መሆናቸው ይታወሳል።
በአካባቢው ነዋሪዎች ዘንድ ከፍተኛ ተቃውሞን ቀስቅሶ በነበረው ግጭት ከ40 የሚበልጡ ፖሊሶችም ድብደባ እንደተፈጸመባቸውና በሆስፒታል ተኝተው ህክምና እየተደረገላቸው መሆኑን በሀገር ውስጥ ያሉ መገናኛ ብዙሃን አክለው ገልጸዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በከተማዋ በተመሳሳይ ሁኔታ ተገንብተዋል ያላቸውን የመኖሪያ አካባቢዎች ለማፍረስ በዝግጅት ላይ መሆኑን ገልጿል።