የካቲት ፰ ( ስምንት )ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- የመን እና ጅቡቲ አገራቸውን ትተው በህገወጥ መንገድ በሚፈልሱ ስደተኞች መጨናነቃቸውን እና ሰብዓዊ ቀውስ መፈጠሩን የዓለም አቀፉ የስደተኞች ድርጅት አይኦኤም አስታወቀ። በእርስበርስ ጦርነት ወደምትታመሰው የመን እና ጅቡቲ በየወሩ ቁጥራቸው ከ10 ሽህ በላይ ስደተኞች በበረሃና በባሕር አቆራርጠው ሕይወታቸውን ለአደጋ አጋልጠው የሚገቡ ሲሆን አብዛኞቹ ፍልሰተኞች ኢትዮጵያዊያን ናቸው።
ወደ የመን ከሚገቡት ስደተኞቹ ውስጥ 30 በመቶ የሚሆኑት እድሜያቸው ለአካለመጠን ያልደረሱ ታዳጊ ወጣቶች ሲሆኑ፣ ጥቂት ሴት ስደተኞች ጨምሮ አንድ ዕድሜው 11 ዓመት የሆነው ታዳጊም እንደሚገኝበት አይኦኤም አስታውቋል። በምስራቅ አፍሪካ ያለው የስደተኞች አያያዝ ሁኔታ ከጊዜ ወደ ጊዜ አስጊ እየሆነ የመጣ ሲሆን፣ የመን የተወሰኑ ኢትዮጵያዊያንን ወደ ጅቡቲ እንዲመለሱ አድርጋለች።ከ4 ሽህ በላይ ኢትዮጵያዊያን ስደተኞች በየመን እስር ቤት ውስጥ በተጨናነቀ ሁኔታ መታሰራቸውን አይኦኤምን ጠቅሶ ቪኦኤ ዘግቧል።