ታህሳስ ፳፱ (ሃያ ዘጠኝ) ቀን ፳፻፮ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- መንግስታዊዎቹ የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እና በሕግ በፈረሰ ድርጅት ስም የሚጠቀመው የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት በጋራ አስጠንተነዋል ባሉት ጥናት መሰረት በአገር ውስጥ ከሚታሙት መጽሄቶች መካከል አዲስ ጉዳይ፣ፋክት፣ሎሚ፣ቆንጆ፣ጃና፣እንቁ እና ሊያ የተባሉ መጽሔቶች ጽንፈኛ ፖለቲካ አራማጆች መሆናቸውን አረጋግጠናል ብለዋል።
አዲስዘመን ጋዜጣ በረቡዕ ታህሳስ 30 ቀን 2006 ዕትሙ መጽሔቶቹ በብዙ ባህርያቸው የጽንፈኛ ፖለቲካ ፓርቲ ልሳናት መሆናቸው፣ በተሳሳቱ መረጃዎች ሕዝቡ በስርኣቱ ላይ እምነት አጥቶ ለአመጽ እንዲነሳሳ የሚያደርጉ ዘገባዎችን ያቀርባሉ ብሏል፡፡
በጥናቱ መጽሔቶቹ የመንግስትን ኃላፊዎች የግል ስብዕና እንደሚነኩ፣የአመጽ ጥሪዎችን እንደሚያሰሙ፣ሽብርተኝነትን እንደሚያበረታቱ፣የፖለቲካ ስርዓቱን እንደሚያጨልሙ፣ኢኮኖሚ ዕድገቱን እንደሚክዱ፣ህገመንግስቱን እንደሚጥሱ በዝርዝር አቅርቧል፡፡
መንግስት መጽሄቶችን በጽንፈኝነት በመፈረጅ ምናልባትም ከ2007 ምርጫ በፊት እንዲዘጉ ሊያደርግ ይችላል ሲል አንድ ያነጋገርነው ጋዜጠኛ ተናግሯል።
“መንግስት ምንም አይነት እርሱ ከሚያራምደው አጀንዳ ውጭ የተለየ ድምጽ መስማት አይፈልግም” የሚለው ጋዜጠኛውም፣ መጽሄቶችን በተለያዩ መንገዶች በመፈረጅ ከገበያ ለማውጣት ያሰበ ይመስላል ሲል አክሎአል።
ኢትዮጵያ የፕሬስ መብቶችን በማፈንና ጋዜጠኞችን በማሰር ግንባር ቀደም ተጠቃሽ ናት። ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ፣ ርእዮት አለሙ፣ ውብሸት ታየ፣ የሱፍ ጌታቸውና ሌሎችም ሀሳባቸውን በመግለጻቸው ብቻ መታሰራቸው ይታወቃል። ከምርጫ 97 በሁዋላ እጅግ ዝነኛ ጋዜጣ ሆነ የወጣው ፍትህ ጋዜጣም በመንግስት ጫና ከገበያ እንዲወጣ ተደርጓል። በጋዜጣው ላይ ሲሰሩ የነበሩት ታዋቂ ጋዜጠኞችም በተለያዩ ክሶች ሲዋከቡ ቆይተዋል።