ኢሳት (ጥር 3 ፥ 2008)
ማክሰኞ በይፋ የተቋቋመንውን የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ምክር ቤትን እንዲመሩ አንድ የመንግስት ባለስልጣን በዋና ፀሃፊነት ተመረጡ።
በሃገር ውስጥ የሚገኙ ጋዜጠኞችንና አሳታሚ ድርጅቶችን ያስተዳድራል የተባለውን ይህንን ምክር ቤት በሃላፊነት ለመምራት የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን ምክትል ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ አብርሃም ገብረመድህን ለምክር ቤቱ ዋና ጸሃፊ ሆነው ተመርጠዋል።
ለጋዜጠኞች መብት መከበርና ለሙያው ድጋፍን ያደርጋል ለተባለው ለዚህ ምክር ቤት የረፖርተር ጋዜጣ ባለቤትና ዋና አዘጋጅ አቶ አማረ አረጋዊ የምክር ቤቱ ሰብሳቢ ሆነው ሲመረጡ፣ ከሸገር ሬዲዮ ጣቢያ ጋዜጠኛ መዓዛ ብሩ ምክትል ሰብሳቢ ሆነው መመረጣቸውን ከሃገር ቤት የተገኘ መረጃ አመልክቷል።
ምክር ቤቱ በይፋ ለማቋቋም በተካሄደው ሰነ-ስርዓት 23 አሳታሚዎችና ብሮድካስተሮች ቢገኙም 18ቱ ብቻ የመመስረቻ ሰነዱን እንደፈረሙ ታውቋል።
ይሁንና አምስቱ አባላት የመመስረቻ ሰነዱን በምን ምክንያት እንዳልፈረሙ የተሰጠ ዝርዝር መረጃ የሌለ ሲሆን ምክር ቤቱን ለማቋቋም ላለፉት አስር አመታት ውይይትና ድርድር ሲካሄድ መቆየቱ ይታወሳል።
ምክር ቤቱን ለማቋቋም ከፍተኛ አስተዋፅዖ ካደረጉ ጋዜጠኞች መካከልም አብዟኞቹ ባለፉት 10 አመታት ውስጥ ከሃገር ተሰደው ይገኛሉ።