ጥር ፰ (ስምንት)ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- ኢህአዴግ “በጥልቀት የመታደስ ንቅናቄውን በፐብሊክ ሰርቪሱ የምንተገብርበት ማስፈጸሚያ እቅድ” በሚል ርዕስ ለመንግስት ሰራተኞች ባዘጋጀው የመወያያ ወረቀት ላይ እንደገለጸው፣ በሲቪል ሰርቪሱ ውስጥ ተቀጥረው የሚሰሩ የመንግስት ሰራተኞች ከዚህ በሁዋላ በአራት ደረጃዎች ተገምግመው ውጤት የሚሰጣቸው ሲሆን፣ ከ1-3 ባሉ ያሉ ደረጃዎችን ለመያዝ አብዮታዊ ዲሞክራሲን ወይም የልማታዊ ዲሞክራሲ አስተሳሰብን በጽኑ ይዞ መታገል ዋና መስፈርት ሆኖ ቀርቧል። ከኢህአዴግ የፖለቲካ ፍልስፍና ውጭ ያሉ ሌሎች አመለካከቶችን የያዙ ሰዎች ዝቅተኛ ነጥብ የሚሰጣቸው በመሆኑ ስራቸውን እስከማጣት ይገደዳሉ።
እያንዳንዱ የመንግስት ሰራተኛ አብዮታዊ ዲሞክራሲን አጥብቆ መያዝ ብቻ ሳይሆን፣ ከኃይማኖት አክራሪነት፣ ከትምክህተኝነት ወይም /ጠባብ/ አመለካከት የፀዳና በግንባር የሚታገል ከሆነ ከፍተኛ ነጥብ ያገኛል። በአንጻሩ አብዮታዊ ዲሞክራሲን ያልያዘ፣ የሃይማኖት አክራሪነት አመለካከት የሚንጸባረቅበት፣ በተግባርም ያለበት፣ አመለካከቱንም የሚደግፍ እንዲሁም ትምክህት ወይም ጠባብ አስተሳሰብ የሚያራምድ ሰራተኛ የመጨረሻው ውጤት የሚሰጠው ሲሆን፣ በስራ ላይ የመቆየት ዋስትናም የለውም።
አዲሱ የእድገት መመዘኛ መስፈረት የመንግስት ሰራተኞችን በሙሉ የኢህአዴግ አባላት እንዲሆኑ የሚያስገድድ ነው። ኢህአዴግ ባቀረበው ወረቀት ላይ የ1 ለ5 ውይይቶች መቆራረጥ የሚታይባቸውና ይዘቱም ላይ ጉድለት የሚታይባቸው ናቸው ብሎአል። በትምህርት ዘረፍ በቀረበው የውይይት ሰነድ ደግሞ በአገሪቱ የትምህርት ጥራት ማምጣት እንዳልተቻለ ይገልጻል።
“ትምህርት ዘርፍ የመማሪያ ማስተማሪያ መጻሕፍት ከህትመት ዝግጅት እስከ ስርጭት ግለፀኝነት የሌለና የተማሪዎችን ቁጥርና መረጃዎች ያላገናዘበ ነው” ሲል ትችት ያቀርባል። የአገሪቱ የትምህርት መጽሃፍት የሚታተሙት የህወሃት ኩባንያ በሆነው ሜጋ አሳታሚ ድርጅት ነው።
በሀገር አቀፍ ፈተና አሰጣጥ በየደረጃው የሚገኙ አካላት “የተፈታኞችን ስም መቀያየር፣ የፎቶ መቀያየር፣ የፊደል ግድፈት፣ የኮድ መቀያየር፣ የፈተና መሰረቅና መሰራጨት” ስህተቶችን እንደሚፈጽሙም የመወያያ ሰነዱ ይገልጻል።
አንዳንድ መምህራን የሃይማኖትና የፖለቲካ አስተሳሰባቸውን በተማሪዎች ላይ ለመጫን እየሞከሩ ነው ሲል ወቀሳ የሚያቀርበው ሰነዱ፣ ኢህአዴግ በእያመቱ ስለሚያደርገው የመምህራንና የተማሪዎች ስብሰባ እንዲሁም ተማሪዎችና መምህራን በአንድ ለአምስት እንዲታቀፉና አብዮታዊ ዲሞክራሲን እንዲሰብኩ ስለሚደርስባቸው ጫና አልገለጸም።