የመንግስት ሰራተኞችን በአመለካከታቸው የሚገመግም አዲስ መመሪያ ተዘጋጀ

መስከረም ፳፫ (ሃያ ሦስት) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-አዲሱ የአቶ ሀይለማርያም ና የአቶ በረከት ስምኦን ጥምር መንግስት የክልልና የወረዳ ባለስልጣናትን በባህርዳር  ከመስከረም 21 እስከ 26 በመሰብሰብ ነው ይህን መገምገሚያ ይፋ ያደረገው።

የስብሰባው አላማ የትራንስፎርሜሽን እቅዱን  ጠንካራና ደካማ ጎኖችን መገምገም የሚል ሲሆን፣ የስብሰባው መፈክር ደግሞ “ዘመቻ መለስ” የሚል እንደነበር ታውቋል።

በአቶ ገዱ አንዳርጋቸው በተመራው ስብሰባ ላይ እንደተገለጸው የሲቪል ሰርቪስ ሰራተኞች ከእንግዲህ ወዲህ  በአዲሱ የውጤት ተኮር መገምገሚያ መሰረት እየተገመገሙ የስራ ውላቸው ይታደስላቸዋል።  በአዲሱ የውጤት ተኮር መገምገሚያ መሰረት አመለካከት የሚለው በኢህአዴግ ካድሬዎች ብቻ የሚሞላ እና 25 በመቶ የሚሆነውን የሚሸፍን ነው።

አመለካከት የሚለው የኢህአዴግን ፖሊሲ መደገፍና የኢህአዴግ አባል መሆን ነው በማለት በስበሰባው ላይ የተሳተፉ አንድ ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ የኢህአዴግ አባል ገልጠዋል።

የኢህአዴግን ፖሊሲ የሚቃወሙ ወይም የተቃዋሚ ድርጅቶች አባላት የሆኑ ወይም የኢህአዴግ አባል ለመሆን ፈቃደኛ ያልሆኑትን በዚህ የግምገማ መስፈርት ከስራ ለማባረር ተብሎ መቀረጹ ታውቋል።

ታዋቂው የአለማቀፍ የሰብአዊ መብት ተማጓች የሆነው ሂውማን ራይትስ ወች ፣ የኢትዮጵያ መንግስት የመንግስት ሰራተኞችን ያለፍላጎታቸው የድርጅት አባላት እንዲሆኑ በማስገደድ ሰብአዊ መብታቸውን ይጥሳል በማለት መክሰሱ ይታወሳል።

___________________________________________________________________________________________________________________________________________________________________________

ESAT is the first independent Ethiopian satellite service tasked to produce accurate and balanced news and information, as well as other entertainment, sports and cultural programming created for and by Ethiopians.

ESAT is committed to the highest standards of broadcast journalism and programming and will strive to provide an outlet of expression to all segments of the diverse Ethiopian community worldwide