(ኢሳት ዲሲ–ሰኔ 11/2010) የመቶ አለቃ በሃይሉ ገብሬ ከእስር ተፈታ።
የመቶ አለቃ በሃይሉ ገብሬ ከ13 አመታት በፊት በሕዝብ የሚደርሰውን ጭፍጨፋ በመቃወም ሔሊኮፕተር ይዘው ወደ ጅቡቲ ከጠፉት የበረራ ባለሙያዎች አንዱ መሆኑ ይታወቃል።
ከአራት አመታት በፊት የታሰረው ሌላው የበረራ ባለሙያ የመቶ አለቃ ማስረሻ ሰጤም በተመሳሳይ ከወህኒ ቤት ወጥቷል።
ይህ በእንዲህ እንዳለም በኤርትራ ወህኒ ቤት ታስረው የነበሩት ኮለኔል ታደሰ ሙሉነህም በቅርቡ መፈታታቸው ታውቋል።
ሰኔ 1 ቀን 1997 በአዲስ አበባ ከተማ የተፈጸመውን ጭፍጨፋ በማውገዝ ሰኔ 5 ኤም አይ 35 የተባለ ሔሊኮፕተር እያባረሩ ጅቡቲ የገቡት የመቶ አለቃ በሃይሉ ገብሬና የመቶ አለቃ አብዮት ማንጉዳይ የጅቡቲ መንግስት አሳልፎ ስለሰጣቸው በአሰቃቂ ወህኒ ቤቶች ማሳለፋቸው ሲዘገብ ቆይቷል።
የመቶ አለቃ አብዮት ማንጉዳይ የ15 አመት እስራቱን በአመክሮ ጨርሶ ከወህኒ ቤት ሲወጣ የእድሜ ልክ እስራት የተፈረደበት መቶ አለቃ በሃይሉ ገብሬ ላለፉት 13 አመታት በወህኒ ቤት አሳልፏል።
የመቶ አለቃ በሃይሉ ገብሬ በምህረት በሳምንቱ መጨረሻ ከተፈቱ በመቶዎች ከሚቆጠሩ እስረኞች አንዱ ሆኗል።
ሌላው የኢትዮጵያ አየር ሃይል ባልደረባና የበረራ ባለሙያ የመቶ አለቃ ማስረሻ ሰጤም በተመሳሳይ ከወህኒ ወጥቷል።
የመቶ አለቃ ማስረሻ ሰጤ በኢትዮጵያ አየር ሃይል ውስጥ ያለውን የብሔር አድሎና ስርአቱን በመቃወም በመንቀሳቀሳቸው ከታሰሩ የበረራ ባለሙያዎች አንዱ ነበር።
በሳምንቱ መጨረሻ ከተፈቱት የህሊና እስረኞች ውስጥ በወህኒ ቤት ከፍተኛ ስቃይ የደረሰባቸው አበበ ካሴና ከፍያለው ተፈራ ይገኙበታል።
ይህ በእንዲህ እንዳለም በኤርትራ ወህኒ ቤት ለአመታት ታስረው የቆዩት ሌተናል ኮለኔል ታደሰ ሙሉነህ በቅርቡ መፈታታቸው ታውቋል።
ኮለኔል ታደሰ ሙሉነህ የኢትዮጵያ አየር ሃይል ባልደረባ የነበሩ ሲሆኑ ወደ ኤርትራ ከተጋዙ 20 አመታት እንዳለፋቸው ታውቋል።