ሚያዝያ ፳፪ (ሃያ ሁለት) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-በመተማ ዮሃንስ ከተማ አስተዳደር የሚገኙ የቀበሌ አስተዳዳሪዎች እና የከተማዋ ፍትህና ጸጥታ ጉዳይ አመራሮች የመሳሪያ ፈቃድ የሚያወጡትን ነዋሪዎች፣ ለመሳሪያ ፈቃድ 260 ብር ፣ ለግዳጅ ቦንድ ግዢ 1 ሺህ ብር
እንዲሁም ለቀበሌ መታወቂያ 300 ብር በማስከፈል ላይ መሆናቸውን ህዝቡን ምሬት ላይ ጥሎታል።
በሱዳኗ የጠረፍ ገበያ ማዕከል በሆነችው የገላባት ቀበሌ በሱቅ እና ምግብ ቤቶች በአስተናጋጅነት የሚሰሩ የመተማ ከተማ ነዋሪዎች እንደተናገሩት ፤ የገዢው መንግስት አመራሮች የእለት ጉርስ ለማግኘት ወደሚችሉበት ገላባት በመሄድ እንዳይሰሩ፣ የመተማ ዮሃንስ መታወቂያ ያልያዘ አይገባም በማለት ሁሉም የቀበሌ መታወቂያዎችን እንዲያዎጡ ማስገደዳቸውን ተናግረዋል፡፡
ከአሁን በፊት ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ወደ ገላባት በመግባት መገበያየት የሚችል እንደነበረ የሚገልጹት ነዋሪዎች ፤በመታወቂያ ሰበብ ገንዘብ ለመሰብሰብ ያዎጡት አዲስ መመሪያ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ባለስልጣናቱ ለመታወቂያ የሚከፈለውን 300 ብር ያለ ደረሰኝ በመቀበል ላይ መሆናቸውን ገልጸዋል።
በከተማዋ ያለውን መብራት ሃይል ለማሳደግ በሚል ከተራ ነዋሪው ጀምሮ እስከ ሆቴል ቤት ነጋዴዎች ከሁለት ሽህ ብር ጀምሮ እሰከ አምስት ሽህ ብር እየተመደበባቸው እንዲከፍሉ መገደዳቸውንም ነዋሪዎች ተናግረዋል፡፡
የከተማ አስተዳደሩ በአነስተኛ ኮንቴይነር የሚነግዱ ጀማሪ ነጋዴዎች ስድስት መቶ ብር ፣ መካከለኛ ነጋዴዎች 4 ሺ 500፣እንዲሁም ከፍተኛ ነጋዴዎች እስከ ስድስት ሺህ ብር መጠየቃቸው ነጋዴዎችን በእጅጉ አበሳጭቷል። የነጋዴዎች ተወካዮች ጉዳዩን ለከተማዋ ከንቲባ አቤት
ቢሉም፣ ከንቲባ አቶ ተሾመ አግማስ “ግዴታችሁ ነው! ክፈሉ!” የሚል ትህትና የጎደለው ምላሽ መስጠታቸው እንዳስከፋቸው ተናግረዋል። ነጋዴዎች የተጠየቁትን ገንዘብ ለመክፈል ፈቃደኞች ሳይሆኑ ቀርተዋል።
የከተማ አስተዳደሩ ካድሬዎች ወደ ነጋዴዎች ቤት በመሄድ ለምርጫ ገንዘብ እንዲያዋጡ ማስገደዳቸው ህዝቡን ለተጨማሪ ምሬት እንደዳረገው ነዋሪዎች ተናግረዋል።