ኢሳት (መጋቢት 13 ፥ 2008)
በተለያዩ ክልሎች የህገ ወጥ መሳሪያዎች ዝውውር መስፋፋትን ተከትሎ የመሳሪያ ዝውውሩን ለመቆጣጠር የሚያስችል አዋጅ (ህግ) እየተዘጋጀ መሆኑን የፌዴራልና አርብቶ አደር ጉዳዮች ሚኒስቴር አስታወቀ።
በጋምቤላ ክልል ብቻ በ13 ወረዳዎች ውስጥ የጦር መሳሪያ ዝውውር መኖርንና ችግሩ ከክልሉ ከፍተኛ የጸጥታ ስጋት መፍጠሩን የክልሉ ባለስልጣናት ገልጸዋል።
ክልሉ ከጎረቤት ደቡብ ሱዳን ጋር የሚዋሰን በመሆኑ በርካታ የህገ ወጥ መሳሪያዎች ዝውውር በክልሉ በመታየት ላይ መሆኑን የጋምቤላ ክልል የጸጥታና አስተዳደር ቢሮ ምክትል ሃላፊ የሆኑት አቶ ቻንክ ፖል ተናግረዋል።
በአማራ ክልልም ከሱዳንና ደቡብ ሱዳን የሚገቡ ህገ-ወጥ የመሳሪያ ዝውውር መኖራቸውን የክልሉ አስተዳደርና የጸጥታ ቢሮ ሃላፊ የሆኑት አቶ ደሴ አስሜ በጉዳዩ ዙሪያ ለመምከር በተጠራ አንድ መድረክ ላይ መግለጻቸውን ከሃገር ቤት የተገኘ መረጃ አመልክቷል።
ባለፉት ሰባት ወራቶች ጊዜ ውስጥ ብቻ 50 ህገ-ወጥ የጦር መሳሪያ አዘዋዋሪዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ሃላፊው የገለፁ ሲሆን፣ በዚህ ዝውውር ምን ያህል መሳሪያ እንደተያዘ ግን የጸጥታ ቢሮ ሃላፊው ዝርዝር መረጃን ከመስጠት ተቆጥበዋል።
ህገ-ወጥ የመሳሪያ ዝውውሩ ለሃገሪቱ ስጋትን ፈጥሮ እንደሚገኝ ያስታወቀው የፌዴራልና አርብቶ-አደር ጉዳዮች ሚኒስቴር በበኩሉ የመሳሪያ ዝውውሩን ለመቆጣጠር የሚያስችል ህግ እየተዘጋጀ መሆኑን ማክሰኞ ገልጿል።
ይሁንና፣ ህጉ መቼ ተግባራዊ እንደሚደረግ ሚኒስቴሩ የሰጠው ዝርዝር አለመኖሩን ከሃገር ቤት ከተገኘ መረጃ ለመረዳት ተችሏል።