የመሬት ፖሊሲው ካልተሻሻለ ህዝባዊ ተቃውሞ ወደ ዕርስ በእርስ ግጭት ሊያመራ ይችላል ተባለ

ኢሳት ( ነሃሴ 5 ፥ 2008)

የኢትዮጵያ መንግስት የመሬት ፖሊሲው ላይ ማሻሻያ የማያደርግ ከሆነ በመካሄድ ላይ ያለው ህዝባዊ ተቃውሞ ወደ ዕርስ በእርስ ግጭት ሊያመራ ይችላል ሲሉ አንድ የተቃዋሚ ፓርቲ አመራር መግለጻቸውን ሮይተርስ ሃሙስ ዘግቧል።

በሃገሪቱ በመስቀለኛ መንገድ ላይ ናት ሲሉ ለዜና አውታሩ የገለጹት የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረስ የሆኑት ዶ/ር መረራ ጉዲና የኢትዮጵያ ህዝብ ገዢው የኢህአዴግ መንግስት ለ25 አመታት በፈጸመው ድርጊት መሰላቸታቸውን አስረድተዋል።

ባለፈው ሳምንት በአካባቢው ተካሄዶ በነበረ ተቃውሞ የወረዳው ነዋሪዎች መገደላቸውን ያወሱት ነዋሪዎቹ ህዝቡ የተነሳውን ጥያቄ ዕልባት እስኪያገኝ ድረስ ትግሉን ለመቀጠል እየተንቀሳቀሰ እንድሆነ አስታውቀዋል።

“ህዝቡ መብቱን በመጠየቅ ላይ እንደሚገኝ ያስታወቁት የፓርቲው አመራር፣ መንግስት የሃይል እርምጃውን አጠናክሮ የሚቀጥል ከሆነ ህዝባዊ አመጹ ወደ ዕርስ በዕርስ ጦርነት ሊያመራ እንደሚችል ያላቸውን ስጋት ለሮይተርስ አስታውቀዋል።

በሳምንቱ መገባደጃ በአማራና ኦሮሚያ ክልሎች በመንግስት የጸጥታ ሃይሎች በተወሰዱ የሃይል ዕርምጃዎች ግድያ ከተፈጸመባቸው ሰዎች በተጨማሪ በሺዎች የሚቆጠሩ ተጨማሪ ነዋሪዎች ለእስር ተዳርገው እንደሚገኙ አቶ መረረ ጉዲና ገልጸዋል።

አዲስ አበባ ከተማን ወደ ኦሮሚያ ክልል ለማስፋፋት የተያዘውን እቅድ ተከትሎ በኦሮሚያ ክልል ከመሬት ባለቤትነት ጋር የተያያዙ ጥያቄዎች በነዋሪው ዘንድ መነሳቱ ይታወሳል።

ይኸው ህዝባዊ ጥያቄ በመንግስት በኩል ተቀባይነት የማያገኝ ከሆነና  በሃገሪቱ የፖሊሲ ማሻሻያዎች ተግባራዊ ካልተደረጉ በመካሄድ ላይ ያለው ተቃውሞ ወደ እርስ በዕርስ ግጭት ሊያመራ ይችላል ሲሉ የኦፌኮ አመራር መግለጻቸውን ሮይተርስ በዘገባው አስነብቧል።

በኦሮሚያ ክልል የተቀሰቀሰው ተቃውሞ በአሁኑ ወቅት ወደ ሌሎች ክልሎች መስፋፋቱን የተናገሩት አቶ መረራ ጉዲና ህዝቡ እራሱን በትብብር እያደረጀ እንደሚገኝ አክለው አስታውቀዋል።

ከመሬት ጋር በተገኛኘ ከወራት በፊት የተቀሰቀሰው ተቃውሞ ጥያቄውንና አድማሱን በማስፋት መንግስት ሊቆጣጠረው ወደማይችለው ደረጃ በመሸጋገር ላይ መሆኑንም አመራሩ ከሮይተርስ ጋር ባደረጉት ቃለምልልስ ገልጸዋል።

ገዥው ኢህአዴግ መንግስት ለአመታት ሲያካሄድ በቆየው የመሬት ማፈናቀል ድርጊት በርካታ ሰዎች ህይወታቸው ወደ ድህነት ማምራቱንና በሃገሪቱ ፍትህሃዊ ስርዓት አለመኖሩን አቶ መረራ ጉዲና በወቅታዊ የኢትዮጵያ ፖለቲካዊ ጉዳይ ጋር በተገኛኘ ቃለመጠይቅ አከለው አስረድተዋል።