መጋቢት ፲፬ (አስራ አራት) ቀን ፳፻፬ ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-መንግስት በቅርቡ ለመምህራን ያደረገውን የደሞዝ ጭማሪ በመቃወም በአዲስ አበባ የሚገኙ በርካታ ትምህርት ቤቶች በትናንትናው እለት የጀመሩት የስራ ማቆም አድማ ዛሬም ለሁለተኛ ቀን ቀጥሎ ውሎአል።
በመምህራን ዘንድ ከፍተኛ ቁጭት እና ስሜት እንዳለ በሚነገርበት በአሁኑ ጊዜ ተቃውሞው ወደ አማራ ክልል ሊሸጋጋር ይችላል በሚል የደህንነት ሀይሎች በአንዳንድ ትምህርት ቤቶች የሚገኙ መምህራንን ሲያስፈራሩ እንደነበር መረጃዎች አመልክተዋል።
በአማራ ክልል በተለይም በባህርዳርና ዙሪያ ወረዳዎች ተመሳሳይ የሆነ የስራ ማቆም አድማ ለማድረግ መምህራን ውስጥ ለውጥ መልእክቶችን መለዋወጣቸውን የአማራ ክልል ዘጋቢያችን ገልጧል።
በአዲስ አበባ የተጀመረውን ተቃውሞ ለማብረድ የመምህራን ማህበር እና የኢህአዴግ ባለስልጣናት ከፍተኛ ርብርብ እያደረጉ ሲሆን፣ መምህራኑ ስራቸውን እየሰሩ ቅሬታቸውን እንዲያቀርቡ ለማግባባት እየሞከሩ ነው።
አንድ ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ መምህር ለኢሳት እንደገለጡት አሁን ለታየው ቁጣ መነሻው የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን የደሞዝ ጭማሪውን አስመልክቶ የሰጠው የዜና ሽፋን እና ይህንን ተከትሎ የቤት ኪራይና ሌሎች እቃዎች በአንድ ሌሊት ጨምረው መገኘታቸው ነው።
አንድ መምህር የደሞዝ ጭማሪ በተደረገ በማግስቱ የቤት ኪራይ በመጨመሩ ምክንያት የቤት እቃውን ሸክፎ የማህበሩ አባላት መጥተው እንዲረከቡት መጠየቁን መምህሩ ገልጠዋል። የመምህራኑን ተቃውሞ የኢህአዴግ አባላት የሆኑ መምህራን ሳይቀር እንደደገፉት ታውቋል። ይሁን እንጅ አገራቀፉ የመምህራን ማህበር የመምህራን ጥያቄ እንደተመለሰ አድርጎ መግለጫ የሰጠ በመሆኑ፣ የአሁኑን የመምህራን ጥያቄ ከሌላ ወገን የመጣ ጥያቄ ለማስመሰል በኢህአዴግ ከፍተኛ ባለስልጣናት በኩል እንቅስቃሴ እየታየ ነው።
ፍትህ ጋዜጣ ዛሬ ባወጣው ዘገባ ወደ 30 የሚጠጉ ትምህርት ቤቶች ስራ አቁመዋል። መምህራኑ በስራ ማቆም አድማው እስከ መቼ እንደሚቀጥሉበት ለማወቅ አልተቻለም። ይሁን እንጅ የኢህአዴግ ባለስልጣናት መምህራን ስራ እንዲጀመሩ ለማግባባት እያደረጉ ያለውን ጥረት መሳካትና አለመሳካቱ የፊታችን ሰኞ የሚታይ ይሆናል። በበርካታ ትምህርት ቤቶች መምህራን ስራቸውን በአስቸኳይ እንዲጀምሩ የሚያሳስቡ ማስታወቂያዎች ተለጥፈዋል።
ኢሳት በአዲስ አበባ አቃቂ ቃሊቲ፣ ኮተቤ፣ አስኮ እና አየርጤና ኮልፌ የሚገኘው ሚሊኒየም ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት፣ ኮልፌ ኮምፕሬሲፍ ሁለተኛና የመሰናዶ ትምህርት ቤት፣ መርካቶ፣ ጎጃም በረንዳ አካባቢ የሚገኘው አጋዚያን ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የሚገኙ መምህራን ስራ ማቆም አድማ አድርገው መዋላቸውን በትናንትና ዘገባው መግለጡ ይታወሳል።
ከአምስት ቀን በፊት የአዲስ አበባ መስተዳደር የትምህርት ቤቶች ርዕሰ መምህራንና የአስተዳደር ሠራተኞችን በማዛጋጃ ቤት ሰብስቦ መምህራን ምንም ዓይነት የሥራ ማቆም አድማና ተቃውሞ እንዳያደርጉ ያስጠነቀቀ ሲሆን ሁኔታው ወደ ፖለቲካዊ ተቃውሞ ተለውጦ አገሪቱ ቀውስ ውስጥ ትወድቃለች ሲል ማስፈራራቱ ይታወሳል።
ከሳምንታት በፊት በሰሜን ጎንደር የሚገኙ ትምህርት ቤቶች የስራ ማቆም አድማ አድርገው እንደነበር ይታወሳል። በስራ ማቆም አድማው የተካፈሉ አንዳንድ መምህራን አሁንም ድረስ ወከባ እየገጠማቸው ነው።
___________________________________________________________________________________________________________________________________________________________________________
ESAT is the first independent Ethiopian satellite service tasked to produce accurate and balanced news and information, as well as other entertainment, sports and cultural programming created for and by Ethiopians.
ESAT is committed to the highest standards of broadcast journalism and programming and will strive to provide an outlet of expression to all segments of the diverse Ethiopian community worldwide