መጋቢት ፲፱ (አስራ ዘጠኝ) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-ቀደም ብሎ ለወ/ሮ አዜብና ቤተሰቦቻቸው መኖሪያ ቤት ግንባታ ተመርጦ የነበረው የስድስት ኪሎው የስብሰባ ማእከል ግቢ፣ አሁን ለመለስ ፋውንዴሽን ህንጻ ማሰሪያ ሊውል መሆኑን ምንጮች ገለጹ።
ወ/ሮ አዜብ እና ሌሎች ከፍተኛ ባለስልጣናት ባለፈው ሀሙስ ስፍራውን ተዘዋውረው የጎበኙ ሲሆን፣ በአካባቢው የሚገኙ መኖሪያ ቤቶችም ከህንጻ ግንባታው ጋር በተያያዘ ሊፈርሱ ይችላሉ፡፡
በከፍተኛ ጥበቃ በስፍራው ላይ የተገኙት ወ/ሮ አዜብ፣ የባለቤታቸውን ፋውንዴሽን በዚሁ ቦታ ላይ ለማሰራት ፍላጎት ያሳዩ አያሳዩ የታወቀ ነገር የለም። ይሁን እንጅ አካባቢውን በተደጋጋሚ መጎብኘታቸው ምናልባትም ቦታውን ለመኖሪያ ቤት ወይም ለፋውንዴሽኑ ጽህፈት ቤት ማሰሪያ ሳይመርጡት እንዳልቀረ ምንጮች ገልጸዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ አቶ ስብሀት የአቶ አባይ ወልዱንና የባለቤታቸውን ለህወሀት ሊቀመንበርነትና ስራ አስፈጻሚነት መመረጣቸውን ተቃውመዋል። አቶ ስብሀት ይህን የገለጹት ከአዲስ አድማስ ጋር ባደረጉት ቃለምልልስ ነው። አቶ ስብሀት ” እኔ በበኩሌ እነዚህ ሁለቱም ሆኑ ሌሎች ሳይተኩ የቀሩ ጥቂት አመራሮች አሁን በወጡትና በሌላ አዲሶች መተካት ነበረባቸው፡፡ ግን ከፍተኛው የህወሓት አካል ጉባኤው፤ ስለመረጣቸው መቀበል ነው ያለብን፡፡ብዙ ነገር አያጐድልም፡፡” ብለዋል። አቶ ስብሀት ከስልጣን የተባረሩት የእነ አቶ አርከበ እቁባይ ደጋፊ ናቸው እየተባሉ ሲታሙ መክረማቸው ይታወሳል። አቶ ስብሀት አቶ አባይ ወልዱ መተካት ነበረባቸው በማለት አቋማቸውን ግልጽ ያደረጉ ብቸኛው የህወሀት ነባር አባል ሆነዋል።