ኢሳት (መጋቢት 22 ፥ 2008)
የቢሊኒየሩ ባለሃብት የሼህ መሃመድ አላሙዲን ንብረት የሆነው ሆራይዘን እርሻ ሃላፊነቱ ይተወሰነ የግል ማህበር ግማሽ ቢሊዮን ብር ቅጣት ተጣለበት። ገንዘቡም ለማህበራዊ አገልግሎት መስሪያ ቤት ገቢ እንዲደረግ ውሳኔ ተላልፏል።
የፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ስምንተኛ ተዘዋዋሪ ከፍተኛ ችሎት የመሃመድ አልአሙዲን ንብረት በሆነው ሆራይዘን እርሻ ሃላፊነቱ የግል ማህበር ላይ ቅጣቱን የወሰነው ከመንግስት የልማት ድርጅቶች ለፈጸመው ግዢ ክፍያ ባለመፈጸሙ እንደሆነ ተመልክቷል።
ጎጀብ እርሻ ልማት፣ ሆራይዘን አዲስ ጎማ፣ ሊሙ ቡና እርሻና፣ በበቃ ቡና እርሻ የተባሉና በመንግስት ይዞታ ስር የነበሩን የእርሻ ልማት ድርጅቶች በግዢ ወደሆራይዘን እርሻ ልማት የለወጡት ሼህ አል አሙዲን ዕዳውን ባለመክፈሉ ቅጣቱ መከተሉን ታውቋል።
ክሶችን የተመለከተው ከፍተኛው ፍርድ ቤት፣ ሆራይዘን እርሻ ልማት ግማሽ ቢሊዮን ብር በአስቸኳይ ለማህበራዊ ግልጋሎት መስሪያ ቤት (Ministry of Public Enterprise) በአስቸኳይ እንዲከፍል ትዕዛዝ ማስተላለፉ ተሰምቷል።
የሚድሮክ እህት ኩባንያ የሆነው ሆራይዘን የእርሻ ልማት ኩባንያ በየጊዜው መከፈል የነበረበትን ክፍያ ሳይፈጽም የቀረው በደረሰበት የገንዘብ ቀውስ ምክንያት እንደሆነና የደረሰበትን ችግር መርምሮ ለማስተካከል የ6 ወር የእፎይታ ጊዜ (grace period) እንዲሰጠው ፍርድ ቤቱን ቢጠይቅም፣ የከፍተኛው ፍርድ ቤት ተዘዋዋሪ ችሎት ላለፉት 8 ወራት ጉዳዩን ሲመረምር እንደቆየና የሚሰጠው የእፎይታ ጊዜ (grace period) እንደሌለ በመግለጽ በድምሩ 433,571,241 እንዲከፍል ወስኗል። ገንዘቡ ሳይከፈል ከተወሰነበት ጊዜ ካለፈም ከእነወለዱ ጭምር ታሳቢ በማድረግ የሚከፈል መሆኑን ለመረዳት ተችሏል።