(ኢሳት ዲሲ–መስከረም 3/2011) የኦሮሞ ነጻነት ግንባር ሊቀመንበርን ለመቀበል የግንባሩን አርማ ማውለብለብም ሆነ አደባባይ መውጣት የሚቻል ቢሆንም የሕዝብ መገልገያዎች ላይ አርማውን ማቅለም ግን የማይቻል መሆኑን የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነር አሳሰቡ።
ፖሊስ ኮሚሽነሩ ይህን ያሉት አቶ ዳውድ ኢብሳን ለመቀበል ከሚደረገው ዝግጅት ጋር ተያይዞ በአዲስ አበባ ወጣቶችና በኦሮሚያ ክልል ወጣቶች መካከል የተፈጠረውን ግጭት ተከትሎ በሰጡት መግለጫ ነው።
ፖሊስ ጣቢያን ጭምር በተቀጣጣይ ነገር ለማቃጠል ሙከራ ታይቷል ያሉት ኮሚሽነሩ ዘይኑ ጀማል ይህ በፍጹም ተቀባይነት የሌለውና በዝምታ የማይታለፍ መሆኑን አሳስበዋል።
የኦሮሞ ነጻነት ግንባር ሊቀመንበር አቶ ዳውድ ኢብሳን ለመቀበል ከሚደረገው ዝግጅት ጋር ተያይዞ በአዲስ አበባ ወጣቶችና በኦሮሚያ ክልል ወጣቶች መካከል የተፈጠረውን ግጭት አስመልክቶ የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነሩ ዘይኑ ጀማል መግለጫ ሰጥተዋል።
ኮሚሽነሩ በመግለጫቸው የግንባሩን አርማ ማውለብለብም ሆነ አደባባይ ይዞ መውጣት መብት ቢሆንም መንገዶችን በኦነግ አርማ ማቅለብ ግን የማይቻል መሆኑን አሳስበዋል።
ይህንንም በማስረዳት በወጣቶቹ በኩል ተቀባይነት መገኘቱን አብራርተዋል።
ፖሊስ ጣቢያን ጭምር በተቀጣጣይ ነገር ለማቃጠል ሙከራ ታይቷል ያሉት ኮሚሽነሩ ይህ በፍጹም ተቀባይነት የሌለውና በዝምታ የማይታለፍ መሆኑን አሳስበዋል።
በአዲስ አበባ ወጣቶች በኩል የኦነግን አርማ በማውረድ የኢትዮጵያን ሰንደቅ አላማ መትከል ታይቷል።ይህም ተገቢ አይደለም ብለዋል።
የአዲስ አበባ ወጣቶች ፈቃጅና ከልካይ መሆን አይችሉም።ሕገወጥ ነገር ከተመለከቱም ለፖሊስ ማሳወቅ ይገባቸዋል ብለዋል ኮሚሽነሩ።
የኦነግ ደጋፊዎችም የሚያደርጉትን ነገር በሕግና ስርአት ካልፈጸሙ ግጭት ሊፈጠር እንደሚችል አሳስበዋል።
በእስካሁኑም ግጭት የድንጋይ መወራወርና ተሽከርካሪ የመስበር አደጋ አጋጥሟል ብለዋል።
ወደ አዲስ አበባ የሚመጡ የኦነግ አመራሮችም ለኦሮሚያ ክልል ወጣቶች ሕግና ስርአትን ባከበረ መልኩ እንዲንቀሳቀሱ ጥሪ ያቀርቡ ዘንድም ጠይቀዋል።