(ኢሳት ዜና–ሕዳር 8/2010) የሕወሃት አመራር የጸረ ዲሞክራሲ አስተሳሰብ ያለበትና ከኢህአዴግ አባል ድርጅቶች ጋርም ያለው ግንኙነት ችግር ያለበት መሆኑን የድርጅቱ ማዕከላዊ ኮሚቴ ገለጸ።
በውዝግብና በቀውስ ውስጥ የቀጠለው የሕወሃት ማዕከላዊ ኮሚቴ ስብሰባውን ሳያጠናቅቅ ሁለተኛውን መግለጫ አውጥቷል።
የድርጅቱ ማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት በመካከላቸው ግለሂስ በማካሄድ ላይ ናቸው።
በኢትዮጵያ የዘር መድሎ አገዛዝ እያራመደ ያለው ሕወሃት የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላቱ በግምገማና በግለሂስ ላይ ይገኛሉ።
መስከረም 22/2010 የጀመረውና በውዝግብና በቀውስ ከ1 ወር በላይ እየተካሄደ ያለው የሕወሃት ግምገማ እስካሁን መቋጫና መጨረሻ አላገኘም።
ምክንያቱ ደግሞ በአሁኑ ጊዜ ያለው ሕዝባዊ እምቢተኝነት የፈጠረባቸው ጫና መሆኑ ነው የሚነገረው።
እንደ ኢሳት ምንጮች ገለጻ የሕወሃት ማዕከላዊ አባላት በሶስት ቡድኖች የተከፈሉ ናቸው።
ባለንበት እየገዛን እንቀጥል፣ለውጥ ካላመጣን ሕልውናችን ያከትማል በሚሉና ሁለቱን የተፋጠጡ ቡድኖች የሚሸመግሉ ናቸው ።
ከማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት ወይዘሮ አዜብ መስፍንና አቶ ብርሃነ ኪዳነማርያም መድረኩን ረግጠው ወጥተዋል።
ሁኔታውን በቅርበት የሚከታተሉት አቶ ነጋሲ ለኢሳት እንደገለጹት ወይዘሮ አዜብ መስፍን ተመልሰው ወደ ስብሰባው ለመግባት ጥያቄ ቢያቀርቡም አልተፈቀደላቸውም ።
የህወሃት ማዕከላዊ ኮሚቴ ግምገማ ከተጀመረ በኋላ ለ2ተኛ ጊዜ የወጣው የድርጅቱ መግለጫ እንደሚያመለክተው የድርጅቱ አመራሮች ጸረ ዲሞክራሲያዊና ለአንድ አላማ የማይታገሉ ናቸው።
እርስ በርስ በመጠቃቃት አንዱ ደግሞ የሜላውን ጥፋት በመከላከል የተመሰረተ ግንኙነት እንዳላቸውም የግምገማው ውጤት ያሳያል።
የአዲሱ ትውልድ አባላትን አመራሩ እንደማይሰጠንና የማብቃት ችግር ያለባቸው መሆኑንም አምነዋል።ከትግሉ ጀምሮ ከበረሃ እስከ እርጅና የቀጠለ አመራር መሆኑን በመግለጽ
በግምገማቸው መግለጫ ላይ ያላነሱትና ይፋ ያላደረጉት ግን ሌብነታቸውን ነው።
ከኢህአዴግ አባል ድርጅቶች ጋር የግንኙነት ችግር እንዳለበት የሕወሃት ማዕከላዊ ኮሚቴ መግለጫ ቢያምንም ዝርዝሩን ግን ከመግለጽ ተቆጥቧል።
ስብሰባው ሲጠናቀቅም ከማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት የሚባረሩና በአዲስ መልክ የሚተኩ እንዳሉ ምንጮቻችን ገልጸዋል።