(ኢሳት ዲሲ–ሐምሌ 10/2010)በአዲስ አበባ ሔንከን ዋልያ ቢራ ፋብሪካ የሚሰሩ ከ2 ሺ በላይ ሰራተኞች ኢዶሚያስ ተብሎ በሚታወቀው የሰው ሃይል አቅራቢ ድርጅት የሚፈጸምባቸውን ብዝበዛና እንግልት በመቃወም ሰላማዊ ሰልፍ አካሄዱ።
ይህ በእንዲህ እንዳለ በሕወሃት የቀድሞ ፖሊስ ኪሚሽነሮች በሚመሩ የሰው ሃይል አቅራቢ ድርጅቶች የገንዘብና የጉልበት ብዝበዛ ይፈጸምብናል ያሉ ከ5 መቶ ሺ የሚበልጡ የልዩ ልዩ መስሪያ ቤቶች ሰራተኞች ለጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ አቤቱታቸውን ማቅረባቸው ተሰምቷል።
ላለፉት 12 አመታት ከሚያስቀጥሯቸው ሰራተኞች ኮሚሽን በማግኘት በሚሊየን የሚቆጠር ገንዘብ የሚሰበስቡት የሰው ሃይል አቅራቢ ድርጅቶች ከሕግና ከስርአት ውጪ ብዝበዛ እየፈጸሙ መሆናቸው ይነገራል።
በአንድ ወቅት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ከእንግዲህ አንዱ ሰርቶ አንዱ ሰርቆ አይኖርም ማለታቸው ይጠቀስላቸዋል።
በአዲስ አበባና አካባቢው በመንግስት ልማት ድርጅቶች እንዲሁም በልዩ ልዩ የመንግስት መስሪያ ቤቶችና ፋብሪካዎች በሰው ሃይል አቅራቢ ድርጅቶች የሚቀጠሩ ሰራተኞች ግን በጠራራ ጸሃይል ተዘረፍን እያሉ እሮሮ ማሰማት ከጀመሩ ሰንብተዋል።
የሄንከን ዋልያ ቢሮ ከ2 ሺ የሚበልጡ ሰራተኞች ተመሳሳይ ብዝበዛ በሰው ሃይል አቅራቢ ኤጀንሲዎች ተፈጽሞብናል በሚል ሰላማዊ ሰልፍ በአዲስ አበባ ከተማ አካሂደዋል።
ኢዶሚያስ በሚባል በቀድሞ የሕወሃት የፖሊስ ኮሚሽነሮች የገንዘብና የጉልበት ብዝበዛ ተፈጽሞብናል ያሉት ሰራተኞች ተቃውሟቸውን በማሰማታቸው የመንግስት መገናኛ ብዙሃንን ትኩረት መሳባቸው ተነግሯል።
የሰራተኛ አቅራቢ ድርጅቶቹ ለሚቀርብላቸው ክስ ምላሽ ከመስጠት ይልቅ ጥያቄ አቅራቢዎቹን እንደሚያሳስሩና እንደሚያሳፍኑ ለማወቅ ተችሏል።
ይህ በእንዲህ እንዳለም ቁጥራቸው ከ5 መቶ ሲህ በላይ የሆኑት እነዚህ ሰራተኞች በተወካያቸው በኩል ለጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ባቀረቡት አቤቱታ እንደገለጹት የሰው ሃይል አቅራቢ ነን በሚሉትና በቀድሞ የሕወሃት የፖሊስ ኮሚሽነሮች በሚመሩት ድርጅቶች ገንዘባቸውንና ጉልበታቸውን እየበዘበዙ ይገኛሉ።
ከእያንዳንዱ ሰራተኛ እስከ 1ሺና 2ሺ በር የሚወስዱት የሰው ሃይል አቅራቢዎቹ ድርጅቶች በሰራተኛው ስም የሚገኘውን አመታዊ ልዩ ጭማሬ እንደሚወስዱም አጋልጠዋል።
ሰራተኞቹ በጥበቃ፣ በጽዳት፣በሹፌርነት በእንግዳ ተቀባይነት እንደሚቀጠሩ ይገልጻሉ።
በሰው ሃይል አቅራቢዎቹ ኮሚሽን እየታሰበ በመሃል ለሚደረግባቸው ብዝበዛ ተመልካች ማጣታቸውንም በአቤቱታቸው ላይ አቅርበዋል።
እናም ከአሁን በኋላም በነሱ ላይ የሚፈጸመው ብዝበዛ እንዲቆም ቀጣሪ ድርጅቶችም ቢሆኑ በቀጥታ ከሰራተኛው ጋር ተገናኝተው ቅጥር እንዲፈጽሙ ይደረግ ወይንም ኤጀንሲዎቹ ይታገዱ ሲሉ ጠይቀዋል።