የላይቤሪያ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ በድጋሚ ተካሄደ

(ኢሳት ዲሲ–ታህሳስ 17/2010)

የላይቤሪያ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ በድጋሚ ተካሄደ።

ባለፈው ጥቅምት በተካሄደው ምርጫ 50 በመቶ ድምጽ ያገኘ ተወዳዳሪ ባለመኖሩ ምርጫው በድጋሚ እንዲካሄድ ተደርጓል።

በምርጫው ታዋቂው የእግር ኳስ ተጫዋች ጆርጅ ዊሃና ምክትል ፕሬዝዳንቱ ጆሴ ቦአካይ ዋና ተፎካካሪዎች መሆናቸው ታውቋል።

በ19ኛው ክፍለ ዘመን ከአሜሪካ ከባርነት ነጻ በወጡ አፍሪካውያን የተመሰረተችው ላይቤሪያ ላለፉት 73 አመታት ሰላማዊ የስልጣን ሽግግር ተደርጎባት አያውቅም።

የአሁኑ ምርጫ ከአንድ በዲሞክራሲያዊ መንገድ ስልጣን ከያዘ ፕሬዝዳንት ወደ ሌላ በሕዝብ ምርጫ ስልጣን ወደሚይዝ ፕሬዝዳንት ሽግግር ሲደረግ በላይቤሪያ ይህ ከረጅም አመታት በኋላ የመጀመሪያ መሆኑ ነው።

የ51 አመቱ ታዋቂው የእግር ኳስ ተጫዋች ጆርጅ ዊሃ ባለፈው ጥቅምት በተደረገው ምርጫ አብላጫ ድምጽ ቢያገኙም ምርጫውን ለማሸነፍ 50 በመቶ ድምጽ አስፈላጊ በመሆኑ አሸናፊ ሳይሆኑ ቀርተዋል።

በመጀመሪያው ዙር ምርጫ ጆርጅ ዊሃ 38 ነጥብ 8 በመቶ ድምጽ ሲያገኙ የ73 አመቱ ጆሴፍ ቦአካይ 28 ነጥብ 8 በመቶ ድምጽ አግኝተዋል።

ይህ ዜና እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስ የምርጫው ውጤት ባይታወቅም በ5ሺ 390 የምርጫ ጣቢያዎች ከጠዋቱ 2 ሰአት ጀምሮ ክፍት ሲሆኑ 2 ነጥብ 1 ሚሊየን የተመዘገቡ መራጮች ድምጽ ይሰጣሉ ተብሎ ይጠበቃል።

ሁለቱም ቀዳሚ ተፎካካሪዎች ጆርጅ ዊሃና ቦአካይ ላይቤሪያን ከገባችበት የኢኮኖሚ ቀውስ ለማውጣት እንዲሁም አዳዲስ የመሰረተ ልማቶችን ለመጀመር ቃል ገብተዋል።

የድጋሚ ምርጫውን ለማካሄድ እቅድ ተይዞ የነበረው ባለፈው ወር ቢሆንም በመጀመሪያው ዙር ምርጫ 3ኛ ደረጃን ይዘው የነበሩት ቻርለስ ብርመስካይን ምርጫው ማጭበርበር ተፈጽሞበታል በማለታቸው ነበር ሳይደረግ የቀረው።

የሀገሪቱ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ግን ማጭበርበር ለመፈጸሙ በቂ ማስረጃ የለም ሲል በመወሰኑ የመጀመሪያው ምርጫን መድገም ሳያስፈልግ ቀርቷል።

የዛሬው ምርጫ የሚደረገው በገና ማግስት በመሆኑ ሕዝቡ አመት በአልን እያከበረ ስለሚገኝ የመራጮች ቁጥር ሊቀንስ ይችላል በሚል ስጋት የምርጫ ኮሚሽኑ ሕዝቡ ድምጽ እንዲሰጥ በመወትወት ላይ ይገኛል።

ተሰናባቿ ፕሬዝዳንትና የኖቤል የሰላም ተሸላሚ የሆኑት ኤለን ጆንሰን ሰር ሊፍ በሚቀጥለው ወር የስልጣን ዘመናቸው ሲያበቃ በዲሞክራሲያዊ መንገድ ለሚመረጥ ፕሬዝዳንት ስልጣኑን ለማስረከብ ምኞታቸውን ገልጸዋል።

ከረጅም ጊዜ የእርስ በርስ ጦርነት በኋላ በ2003 በአማጽያን ከስልጣን የተወገዱት ቻርለስ ቴይለር በጎረቤት ሴራሊዮን በፈጸሙት የጦር ወንጀል በሔግ በሚገኘው አለም አቀፍ የወንጀለኞች ችሎት የ50 አመት እስራት ተፈርዶባቸው በእንግሊዝ እስር ቤት ይገኛሉ።