የሉቴኒያ ኩባንያ የኢትዮጵያ ተዋጊና እቃ-ጫኝ አውሮፕላኖችን ሊጠግን ነው

ኢሳት (መጋቢት 9 ፥ 2008)

መቀመጫውን በቀድሞ ሶቪየት ህብረት ስር በነበረችው ሉቴኒያ ያደረገ አንድ የአውሮፕላን ቁሳቁሶች አቅራቢ ኩባንያ የኢትዮጵያ አየር ሃይል ተዋጊና እቃ ጫኝ አውሮፕላኖች ለመጠገን ስምምነት ፈፀመ።

ይኸው ኤፍ-ኤል-ቴክኒክስ (FL-Technics) የተሰኘው ተቋም ኤሮ L-39 የተሰኙ የመለማመጃ ጀቶች እንዲሁም ሁለገብ ለሆኑ አንቶኖቭ አውሮፕላኖችና ተዋጊ አውሮፕላኖች መለዋወጫ እቃዎችን እንደሚያቀርብ ገልጿል።

የተደረገውን የገንዘብ ስምምነት ከመግለጽ የተቆጠበው ኩባንያው እድሜ ጠገብ የሆኑ አውሮፕላኖች ለመጠገን የሚረዳው የመለዋወጫ ቁሳቁስ በቀጣዩ ሁለትና ሶስት ወራቶች ውስጥ ወደ ኢትዮጵያ ተጠቃለው እንደሚገቡም ባወጣው መግለጫ አመልክቷል።

የመለዋወጫ ቁሳቁሶች ይቀርብላቸዋል የተባሉት የኢትዮጵያ አየር ሃይል የተለያዩ አውሮፕላኖች ስሪታቸው በ1960 እና በ1970ዎቹ ውስጥ በአሁኗ ሩሲያ መሆኑንም ከድርጅቱ መረጃ ለመረዳት ተችሏል።

ከኢትዮጵያ ጋር የተደረገው ስምምነትም በቀጣይ የሚደረጉ ትብብሮችን እንደሚያጠናክርና በኢትዮጵያ መከላከያ ሚኒስቴር ዘንድ እምነትን ለማግኘት የሚረዳ እንደሆነ የኩባንያው የበላይ ሃላፊ የሆኑት ዚልቪናስ ላፒናስካስ አስታውቀዋል።

የተወሰኑ የመለዋወጫ እቃዎች ወደ አዲስ አበባ መድረሳቸውን ያወሱት ሃላፊዎች የተቀሩ ቁሳቁሶችም ከዋናው መስሪያ ቤትና በሌሎች ሃገራት ከሚገኙ ቅርንጫዎች ተሰብስቦ ለሃገሪቱ እንደሚቀርብ ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ አየር ሃይል ውስጥ በማገልገል ላይ ያሉ አብዛኞቹ የጦር ጀቶችና የወታደራዊ እቃ ማጓጓዣ አውሮፕላኖች አብዛኞቹ እድሜ ጠገብና ሩሲያ ሰራሽ መሆናቸው ይነገራል።

እነዚሁ አውሮፕላኖች ጥቅም ላይ ለማቆየት መንግስት በሚሊዮን የሚቆጠር ዶላርን ወጪ እንደሚያደርግም ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው አካላት ይገልጻሉ።

ጥገና ይደረግላቸው የተባሉ ሁለገብ አንቶኖቭ አውሮፕላኖች መካከል AN-32 የሚል ስያሜ ያለው ሲሆን ይኸው አውሮፕላን ዋጋው ወደ 10 ሚሊዮን ዶላር እንደሚደርስና የመለዋወጫ እቃዎቹም ውድ እንደሆኑ መረጃዎች የመለክታሉ።