ጥቅምት ፳፬ (ሀያ አራት) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-በአዲስ አበባ ዙሪያ በሚገኘው የገጣፎ ለገዳዲ ከተማ ነዋሪዎች ትናንት ባካሄዱት ስብሰባ በአካባቢያቸው ስለሚፈጸመው ሙስና ከአካባቢውና ከክልል ባለስልጣናቱ ጋር ክርክር አካሂደዋል።
ከ1000 በላይ ተሰብሰባዎች በተገኙበት በዚህ ስብሰባ ህብረተሰቡ በአካባቢው ስለሚካሄደው የመሬት ዝርፊያ ብሶቱን እያወጣ አሰምቷል።
በስብሰባው ላይ ከቀረቡት ጥያቄዎች መካከል ” 90 በመቶ የሚሆነው የአካባቢው ህዝብ ካርታ ሳይሰጠው፣ ከ 18 ሺ የሚደረስ ካርታ ለማን ተሰጠ ? ይህን ካርታ የያዙት ሰዎች ስም ዝርዝር ለምን ይፋ አይደረግልንም፣ መሬት እየሸነሸኑ ከእናንተ ጋር ሲሸጡ የነበሩት መሀንዲስ ወደ አገር ተመልሰው ለፍርድ እንዲቀርቡልን” የሚሉት ይገኙበታል።
ነዋሪዎች “በአንድ ሰው ስም 20 ካርታዎች መሰጠታቸውን ፣ ይህንን ዝርፊያ ለመቃወም ድምጻቸውን ያሰሙ ወጣቶች የፖለቲካ አጀንዳ ያራምዳሉ በማለት ክስ መቅረቡ ተቀባይነት የሌለው ነገር መሆኑን” ለባለስልጣናቱ ገልጠዋል።
በ2004 ዓም ህዳር ወር ላይ የከተማው የቀበሌ ሊቀመንበር የነበሩ ሰው፣ ባለ ሁለት ፎቅ ቤት ገንብቶ በከፈተው ሆቴል የምረቃ በአል ላይ፣ ሌላ የወረዳው ባለስልጣን አንድ ውስኪ በ60ሺ ብር ተጫርቶ መግዛቱን የመንግስትና የህዝብ ሀብት ምን ያክል እየተመዘበረ መሆኑን ያሳያል በማለት ህዝቡ በመረጃነት አቅርቧል።
ስብሰባውን የመሩት ከኦሮምያ ክልል የተወከሉት አቶ ኢብራሂም ሀጂ ፣ የከተማው ከንቲባ አቶ ገለታ መገርሳ ፣ የወረዳው የኦህዴድ ሃላፊ አቶ ጨምር ኦልቀባ ናቸው። ባለስልጣናቱ ለተነሱት ጥያቄዎች መልስ ለመስጠት ተቸግረው እንደነበር ስብሰባውን የተከታተለው ዘጋቢያችን ገልጧል።
የከተማው ምክር ቤት ከህዝብ ጎን በመቆም ሲያስተባብር እንደነበር ለማወቅ ተችሎአል።