የህግ ባለሙያው አቶ ተሾመ ገብረማሪያም የቀብር ስነስርዓት ረቡዕ በቅድስ ስላሴ ካቴድራል ተፈጸመ

ኢሳት (ታህሳስ 13 ፥ 2009)

የታዋቂው ኢትዮጵያ የህግ ባለሙያ የአቶ ተሾመ ገብረማሪያም የቀብር ስነ-ስርዓት በቅድስት ስላሴ ካቴድራል ተፈጸመ። በ86 አመታቸው ድንገት ከዚህ አለም በሞት መለየታቸው የተገለጸው አቶ ተሾመ ገብረማሪያም በአጼ ሃይለስላሴ ዘመነ መንግስት በጠቅላይ አቃቤ-ህግነት እንዲሁም የማዕድን ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ሆነው አገልግለዋል።

የቀዳማዊ ሃይለስላሴ መንግስት ሲወገድ ወደ እስር ቤት ከተጋዙት የመንግስት ባለስልጣናት አንዱ የነበሩት አቶ ተሾመ ገ/ማሪያም ለ8 ዓመታት በወህኔ ካሳለፉ በኋላ፣ የጥብቅና ድርጅት መስርተው በዚሁ ዘርፍ ከፍተኛ የማማከር ስራ ሲሰሩ መቆየታቸው በህይወት ታሪካቸው ላይ ተመልክቷል። በዚሁ ዘርፍ የማማከር ስራቸውን በሰሜን አሜሪካ ጭምር ያካሂዱ እንደነበርም መረዳት ተችሏል።

በምርጫ 97 ማግስት የቅንጅት መሪዎች ወደ ወህኒ በተጋዙበት ወቅት፣ ለተከሳሾቹ በነጻ ጠበቃ ለመሆን ከተንቀሳቀሱ የህግ ባለሙያዎች አንዱ እንደነበሩ ይታወሳል።

ታህሳስ 12 ቀን 2009 በአዲስ አበባ ቅድስት ስላሴ ካቴድራል አስከሬናቸው ያረፈው አቶ ተሾመ ገ/ማሪያም የአንዲት ልጅ አባት እንደነበሩም ለመረዳት ተችሏል።