የህገወጥ  የሰዎች  ዝውውር  ሰለባ   የሆኑ ስደተኞች  አርብ እለት  ወደ ሰሜን ሱዳን ሲጓዙ  በመኪና አደጋ ህይወታቸው አለፈ።

የካቲት ፴(ሠላሳ) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- ሱዳን ትሪቢዩን የዓይን ምስክሮችን ጠቅሶ እንደዘገበው ከሟቾቹ መካከል አብዛኞቹ ኢትዮጵያውያን ሲሆኑ፤ ከህገ ወጥ አሻጋሪዎቹ መክከል ሁለቱ ህይወታቸው ማለፉ ተመልክቷል።

እንደ ሱዳን ፖሊስ ገለጻ አደጋው የደረሰው ከካርቱም 79 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘውና አል-ባካ ተብላ በምትጠራው አካባቢ  ባለው “የሺሪያን  አል-ሺማጅ” የቀለበት መንገድ ላይ ነው። እስካሁን  ከተጎጆዎቹ መካከል 15ቱ መሞታቸው ታውቋል።

አሽከርካሪዎች  ብዙውን ጊዜ ከተፈቀደው ፍጥነት በላይ  የሚያሽከረክሩበት ይህ የቀለበት መንገድ ፤ ቀደም ሲልም ተደጋጋሚ አደጋውችን እንዳስተናገደ የፖሊስ ሪፖርት ያመለክታል። በመሆኑም  ከተገቢው ፍጥነት በላይ የሚያሽከረክሩትን ከመቅጣት በተጓዳኝ  በቀለበት መንገዱ ላይ ፍጥነት የሚያነብ ኤሌክትሮኒክ ቦርድ ለመስቀል ንቅስቃሴ መጀመሩን የሱዳን ፖሊስ አስታውቋል።

ዓለማቀፉ  የሰብ አዊ መብት ተሟጋች- ሂዩማን ራይትስ ዎች የሱዳንን እና የግብጽ ፖሊሶችን በህገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር  ይከሳቸዋል። የዓይን ምስክሮች ለሱዳን ትሪቢዩን እንደተናገሩትም የሁለቱ ሀገራት ፖሊሶች ህገ-ወጥ አሻጋሪዎቹን ሲይዙ ከማሰር ይልቅ ከነሱ ጋር በመተባበር ሁኔታዎችን እንደሚያመቻቹ ነው የተናገሩት።

በአፍሪካ ህብረት፣  በተባበሩት መንግስታት  የስደተኞች ጉዳይ ከፍተኛ ኮሚሽነር፣ በ ዓለማቀፍ የስደተኞች ድርጅትና በሱዳን መንግስት  ትብብር ባለፈው ጥቅምት ወር ሱዳን  ህገወጥ  የሰዎች ዝውውር በሚገታበት መንገድ ዙሪያ የመከረ ዓለማቀፍ ኮንፈረንስ  የተካሄደ ሲሆን፤ በኮንፈረንሱ  15 ሀገሮችና የአውሪፓ ህብረት ተወካዮች ተገኝተዋል።