የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሚኒስትሮችን ሹምሽር ጨምሮ የተለያዩ አዋጆችን እንደሚያፀድቅ ተነገረ

ኢሳት (ሃምሌ 18 ፥ 2008)

ከሁለት ሳምንት በፊት የ2008 አም የስራ ዘመኑን አጠናቆ ለእረፍት የተበተነው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ማክሰኞ የጠራው አስቸኳይ ስብሰባ የሚኒስትሮችን ሹምሽር ጨምሮ የተለያዩ አዋጆችን ማጽደቅ እንደሚያካትት ሪፖርተር ዘገበ።

ከአምስት አመት በኋላ ፓርላማው ጠርቶታል የተባለው ይኸው አስቸኳይ ስብሰባ ሶስት አዋጆችን ያጸድቃል ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን፣ ጠቅላይ ሚኒስተር አቶ ሃይለማሪያም ደሳለኝ በተወሰኑ ሚኒስትሮች ላይ ያደረጉት ሹምሽር እንዲጸድቅላቸው እንደሚያደርጉም በሪፖርተር ዘገባ ተመልክቷል።

ማክሰኞ በሚካሄደው አስቸኳይ የፓርላማ ስብሰባ በቅርቡ የተዋወቀውን የገቢ ግብር ረቂቅ አዋጅ፣ የተሻሻለውን የንግድ ምዝገባና እና የታክስ አስተዳደር ረቂቅ አዋጅ ያፀድቃል ተብሎ እንደሚጠበቅም የመንግስት መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል።

ረቂቅ አዋጆቹ ፓርላማው ለእረፍት ከመበተኑ በፊት ቀርበው የነበረ ቢሆንም አዋጆቹ ሰፊ ውይይትን የሚፈልጉ በመሆናቸው እስካሁን ድረስ ለውሳኔ ሳይቀርቡ መቅረታቸው ተገልጿል።

የህዝብ ተዋካዮች ምክር ቤት በዚሁ ልዩ እና አስቸኳይ ስብሰባው ሶስቱ ህጎችን ከማጽደቁ በተጨማሪ የሚኒስትሮች ሹም ሽርን ያካሄዳል ተብሎ ይጠበቃል።

ይሁንና፣ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ሃይለማሪያም ደሳለኝ በፓርላማ ስለሚያጸድቋቸው አዳዲስና ተሰናባች ሚኒስትሮች የተሰጠ ዝርዝር መረጃ የለም።

በገቢ ግብር ላይ በቅርቡ የተላለፉ አዳዲስ አዋጆችና ንግድን ለመጀመር በመነሻነት በሚያስፈልጉ ካፒታሎች ላይ ፓርላማው ድምፅን ይሰጣል ተብሎ እንደሚጠበቅ ለመረዳት ተችሏል።