ጥር ፳፯(ሃያ ሰባት) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-<<በየክልሉ የሚገኙ የህዝብና የመንግስት የልማት ድርጅቶች፤ የባለስልጣናት መሸሸጊያ ናቸው>> ሲል የመንግስት ኮሙነኬሺን ቢሮ ባሰባሰበው የምርጫ ድጋፍ የህዝብ አሰተያየት አመለከተ፡፡
በልማት ድርጅት ስም የብአዴን፣የህወሀትና የኦህዴድ ንብረቶች በሆኑት እነኚህ ድርጅቶች ላይ ለስራ የሚመድቡት በ አመዛኙ በየድርጅቶቹ ውስጥ ጥፋት ፈጽመው እርምጃ ይሚወሰድባቸው የድርጅት አባላት መሆናቸውን ያመለከተው የኮሙኒኬሽን ቢሮ፤ ድርጅቶቹ የሙሰኛ ባለስልጣናት መሸሸጊያ ዋሻ መሆናቸውን አመልክቷል። የህወሀቱ ኢፈርት፣ የብአዴኑ ጥረትና የኦህዴዱ ዲንሾ በስራቸው በርካታ የንግድ ተቋማትንና ኩባንያዎችን ይሚያንቀሳቅሱ ሲሆን፤በሀብት ህወሀት የአንበሳውን ድርሻ እንደያዘ ይታወቃል።
የአጥፊ ሹመኞች መሸሸጊያ ከተባሉት መካከል በአማራ ክልል ያሉት ጥረት ኢንዶውመንት ፤ዳሸን ቢራ ፋብሪካ ፤ ዘለቀ እርሻ ልማት ፤ ጋፋት ኢንዶውመንት ፤ ጣና ሞባይል ፡ የአማራ ክልል ፕላስቲክ ፋብሪካ ፤የገጠር መንገዶች ድርጅት ፤ የውሃ ስራዎች ኮንስትራክሺን ድርጅት ፤ የከተማ ልማት ፤ የኢትዮጵያ ቃጫ ውጤቶች ድርጅት መጋዘን፤የኢትዮጵያ ማእድን ልማት አክሲዮን ማህበር፤የባህርዳር ጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካ፣ የኮምቦልቻ ጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካ፣ የግብርና መካናይዜሽን አገልግሎት ድርጅት፣ የትራንስፖርት ኮንስትራክሽን ዲዛይን አክሲዮን ማህበር እና ቪልቶ ሲራሮ እርሻ ልማት እና ዱከም ጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካ ይገኙበታል።
በኢፈርት ስም ባሉትም አያሌ ድርጅቶች ይሚመደቡት ሰዎች በህወሀት ውስጥ አጥፍተው የዲሲፒሊን ቅጣት የሚጣልባቸው አባላት ናቸው ያለው ቢሮው፤ ተቋማቱ እየተመሩ ያሉት በጥፋተኛ የድርጅት አባላት መሆኑን ገልጿል።