የህወሃት/ኢህአዴግ መንግስት የድረገጾች ጠለፋ ተፈጽሞብናል አለ

ኢሳት (መጋቢት 21 ፥ 2008)

የረቀቁ የኢንተርኔት የስለላ ተግባሮችን እንደሚጠቀም የተለያዩ መረጃዎች ሲቀርቡበት የቆየው የኢትዮጵያ መንግስት በሌላ ሃገር በመንግስታዊ ድረ-ገጾች ላይ የጠለፋ (የሃኪንግ) ተግባር ተፈጽሞብኛል ሲል አስታወቀል።

ይኸው ድርጊት በኦሮሚያ ክልል የተቀሰቀሰውን ተቃውሞ ተከትሎ መፈጸም መጀመሩን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የኢንፎሪሜሽን ቴክኖሎጂ ሚኒስትሩ ዶ/ር ደብረፂዮን ገብረሚካዔል ለፓርላማ ባቀረቡት ሪፖርት ይፋ አድርገዋል።

በሚኒስቴር መስሪያ ቤታቸው ዙሪያ ሰሞኑን ለፓርላማ ሪፖርትን ያቀረቡት ዶ/ር ደብረጽዮን በሌላ ሃገር ተፈጽሟል ያሉት የድረ-ገጾች ጥቃት (ሰበራ) በወረዳ-ኔት ድረ-ገጽ ላይ ያተኮረ እንደነበር አስታውቀዋል።

ሚኒስትሩ ጥቃቱ ከየትኛው አገር እንደተሰነዘረ መታወቁን ቢገልጹም የሃገራቱን ስም ከመግለጽ መቆጠባቸውን ከሃገር ቤት የተገኘ መረጃ አመልክቷል።

ችግሩ በኦሮሚያ ክልል የተቀሰቀሰውን ተቃውሞ ተከትሎ መፈጸሙን ለፓርላማ ያስታወቁት ዶ/ር ደብረጽዮን፣ መንግስት ጉዳዩን ልዩ ትኩረት ሰጥቶበት እየተከታተለው እንደሚገኝም ተናግረዋል።

በሌላ ሃገር ጥቃት ተፈጽሞባቸዋል የተባሉት የመንግስት ድረ-ገጾችም በአሁኑ ሰዓት ችግራቸው ተፈትቶ አገልግሎትን እየሰጡ እንደሚገኝ የኢንፎሜሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትሩ አክለው ገልጸዋል።

በመንግስታዊ ድረ-ገጾች ላይ የተፈጸመው የሃኪንግ ጥቃትም በሃገሪቱ የተፈጠረውን ችግር በማራገብ ለማቀጣጠል መሞከር እንደነበር ዶ/ር ደብረጽዮን ለፓርላማ ባቀረቡት ሪፖርት አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ መንግስት ከአንድ የጣሊያን ድረ-ገጽ ጠለፋ (ሃኪንግ) ኩባንያ ጋር ግንኙነት በመፍጠር  በኢንተርኔት የስለላ ተግባር ላይ ተሰማርቶ መቆየቱን የተለያዩ አካላት ይፋ ሲያደርጉ መቆየታቸው ይታወሳል።

መቀመጫውን በካናዳ ያደረገ የቴክኖሎጂ ኩባንያ የተለያዩ ማስረጃዎችን ዋቢ በማድረግ የኢትዮጵያ መንግስት አለም አቀፍ ህግን የጣሱ የኢንተርኔት የስለላ ተግባር ሲፈጸም መቆየቱን መጋለጡን ዋሽንግተን ፖስት ጋዜጣን ጨምሮ ሌሎች አለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል።

መረጃው ይፋ መደረግ ተከትሎ ከመንግስት ጋር ግንኙነት እንዳቋረጠ ይፋ ያደረገው የጣሊያኑ ኩባንያም አገልግሎቱን ለማቅረብ ከአንድ ሚሊዮን ዶላር በላይ ክፍያ እንደተቀበለ ማረጋገጡም የሚታወቅ ነው።

ይሁንና፣ ኩባንያው አገልግሎቱን ሲሰጥ የቆየው ለደህንነት ስራዎች ብቻ እንደነበር አስታውቆ ደንበኞቹ አገልግሎቱን የሰብዓዊ መብት ጥሰትን ለመፈጸም እንደሚጠቀሙበት ገልጿል።

ይህ በእንዲህ እንዳለም የኢትዮጵያ ትምህርት ሚኒስቴር ድረ-ገጽ በ75 ሺህ ሰዎች በመጎብኘት ቀዳሚ ሲሆን የመንግስት ኮሚኒኬሽን ጽ/ቤት በ41 ሰዎች መጎብኘቱን ለፓርላማ ከቀረበው ሪፖርት ለመረዳት ተችሏል።