ኢሳት (ጥቅምት 14 ፥ 2009)
በኢትዮጵያ በስልጣን ላይ የሚገኘው ገዢው የኢህአዴግ መንግስት የህዝቡን ጥያቄ በመቀበል ከስልጣን መውረድ እንዳለበትና በሃገሪቱ የሽግግር ስርዓትና የህገ-መንግስት ረቂቅ እንደሚያስፈልግ በአሜሪካ ዋሽንግተን ዲሲ ከተማ የተካሄደው የምሁራን ጉባዔ አስገነዘበ።
የቪዥን ኢትዮጵያ ፕሬዚደንት ፕሮፌሰር ጌታቸው በጋሻው የጉባዔውን መጠናቀቅ አስመልክተው ለኢሳት እንደገለጹት “ህወሃት የሚመራው መንግስት ህዝብን እየገደለና ሰብዓዊ መብት እየረገጠ በመሆኑ ስልጣኑን ሊለቅ ይገባል።
በቪዥን ኢትዮጵያና በኢሳት ትብብር በሳምንቱ መገባደጃ ቅዳሜና እሁድ የተዘጋጀው ኮንፈረንስ ሲጠናቀቅ እንደተገለጸው አሁን ባለው የኢትዮጵያ ሁኔታ የሽግግርና አዲስ ህገመንግስት ያስፈልጋል።
በኮንፈረንሱ ማጠቃለያ ላይ በኢትዮጵያ አዲስ ስርዓት ለማበጀት የሽግግር ካውንስል ማቋቋም እንደሚያስፈልግ መግባባት ላይ መደረሱ ተገልጿል።
የቪዥን ኢትዮጵያ ዋና ጸሃፊ ዶ/ር አሸናፊ ጎሳዬ ለኢሳት እንደገለጹት፣ የሰላም ሚና ያለውና ሃገሪቱን ወደ ሽግግር ሂደት የሚወስደው ካውንስል የተለያዩ አካላት እንዲወስኑበት ማድረግ ያስፈልጋል።
አሁን ያለው ገዢ ፓርት ህወሃት/ኢህአዴግ ግድያውን እንዲያቆምና ለሰላም በሩን በመክፈት ለድርድር ፈቃደኛ እንዲሆን ጥሪ መተላለፍን ገልጸዋል።
ዶ/ር አሸናፊ እንዳሉት በኢትዮጵያ በተካሄደው ግድያና የሰብዓዊ መብት ረገጣ እጃቸው ያለበት ባለስልጣናት ማንኛውም የገዢው ፓርቲ አባላት በህግ መጠየቅ ይኖርባቸዋል።
በቪዥን ኢትዮጵያ የተካሄደውን ስብሰባ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን በፌስቡክና በኢሳት ድረገጽ ቀጥታ ስርጭት መከታተላቸው ታውቋል። የስብሰባውን አጠቃላይ መግለጫና የተደረሰበትን ድምዳሜ ቪዥን ኢትዮጵያ በቅርቡ ይፋ እንደሚያደርግ ተገልጿል።