ሚያዚያ ፳፪ (ሃያ ሁለት) ቀን ፳፻፬ ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-በአካባቢው ከፍተኛ ውጥረት ነግሷል ተብሎአል።“ጅንግራ”ተብላ የምትጠራውና የመተማ አካል የሆነችው የኮንትሮባንድ መናኸሪያ ሰፈር ፤ በአቶ መለስ መንግስት ታጣቂዎች ሙሉ በሙሉ በእሳት መውደሟ ተገለጸ።
መንደሯ በውስጧ ያቀፈቻቸው ከ 50 የሚበልጡ መኖሪያ ቤቶች፤ ከነንብረቶቻቸው ሙሉ በሙሉ መውደማቸውን ከስፍራው የወጡ ዜናዎች አመልክተዋል።
የዜናው ምንጮች ከስፍራው ያስተላለፉት መረጃ እንደሚያመለክተው፤ የኢትዮጵያ መንግስት ጅንግራን ፦’ለልማት እንደሚፈልገው በመግለጽ የ አካባቢው ነዋሪዎች ስፍራውን ለቅቀው እንዲነሱ በተደጋጋሚ ያደረገው ሙከራ፤ በህዝቡ እምቢተኝነት ሲከሽፍበት ቆይቷል።
የመተማ ከተማ አንድ አካል የሆነችው “ጅንግራ” በስተ ሰሜን ምዕራብ አቅጣጫ ከሚገኘውና “ገላቫት” ከሚባለው የሱዳን የድንበር ከተማ ጋር የተገናኘ ሲሆን፤ከሱዳን ወደ መተማ የሚገባው ነዳጅ፣ ልባሽ ጨርቆች፣የፕላስቲክ ውጤቶች እና የፋብሪካ ምርቶች ወደ መሀል አገር የሚገቡት እዚህ ቦታ ላይ ካረፉ በሁዋላ ነው።
በአንፃሩ ከ ኢትዮጵያ ወደ ሱዳን የሚላኩ ሸቀጣሸቀጦች፣የ አልኮል መጠጦች፣ ቡና፣ጥራጥሬዎች እና ሌሎች የምግብ እህሎች የሚተላለፉት በዚሁ ስፍራ እንደሆነ የዜናው ምንጮች ገልጸዋል።
ከዚህ አንፃር ቦታው በርካታ ሱቆችን፣መጋዘኖችን፣ቡና ቤቶችንና ሌሎች የንግድ ድርጅቶችን ጭምር ያቀፈ ነበር ያሉት በስፍራው የሚገኙ ምንጮች፤ ህወሀት፤ በአካባቢው የነበሩ ነዋሪዎችን በማንሳት- ይህን ስፍራ የራሱ ለማድረግ የተለያዩ ሙከራዎችን ሲያደርግ መቆየቱን አስታውሰዋል።
ህወሀት መራሹ መንግስት ቦታውን ለራሱ ለመውሰድ ያደረገው ጥረት በህዝብ እምቢተኝነት ሲከሽፍበት፤ ትናንት ሌሊት መንደሩን በ እሳት በማጋዬት የሰው ልጅ ሊፈጽመው የማይችለውን አረመኔያዊ ድርጊት ፈጽሟል ሲሉ ምንጮቹ ተናግረዋል።
በቃጠሎው ከ 50 በላይ ቤቶችና የንግድ ተቋማት እስከያዙት ንብረት ሙሉ በሙሉ መጋየታቸውንና በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠር ንብረት መውደሙንም አመልክተዋል።
ይሁንና በሰው ህይወት ላይ ስለደረሰ ጉዳት በዜናው የተገለጸ ነገር የለም።
ምንጮቹ እንዳሉት በአሁኑ ሰዓት የመተማ ህዝብ ቁጣውን በሥርዓቱ ላይ እየገለፀ ሲሆን፤ መንግስትም ሁኔታው ከቁጥጥር ውጪ እንዳይሆን በሚል ስጋት በአካባቢው የጸጥታ ሀይሉን እያጠናከረ ይገኛል።
ከተፈፀመው አስደንጋጭ ክስተት ጋር ተያይዞ በአካባቢው አስፈሪ ውጥረት መንገሱን የገለፁት ምንጪቹ፤ በቀጣይ የሚሆነውን ነገር ከስፍራው እየተከታተሉ መረጃውን እንደሚያደርሱ አስታውቀዋል።
ኢሳት ዘገባውን ለማጣራት መኩራ በማድረግ ላይ ነው። ሙሉ መረጃው እንደደረሰን እናቀርባለን።
___________________________________________________________________________________________________________________________________________________
ESAT is the first independent Ethiopian satellite service tasked to produce accurate and balanced news and information, as well as other entertainment, sports and cultural programming created for and by Ethiopians.
ESAT is committed to the highest standards of broadcast journalism and programming and will strive to provide an outlet of expression to all segments of the diverse Ethiopian community worldwide