የህንዱ ፓወር ግሪድ ከ 400 ሚሊዮን ብር በላይ ገንዘብ ተከፍሎት ስራውን ለቀቀ

መስከረም ፮ (ስድስት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሃይል ድርጅትን እንዲያስተዳደር ለሁለት አመታት 21 ሚሊዮን 700 ሺ ዶላር ወይም ከ400 ሚሊዮን ብር በላይ የተከፈለው ፓወር ግሪድ ይህ ነው የሚባል ስራ ሳያከናውን ተሰናብቷል።
በአገሪቱ ውስጥ የሚታየው የመብራት መጥፋት ሊሻሻል ካለመቻሉ ጋር ተያይዞ፣ ቀድሞውንም ይህን ያክል ገንዘብ ማውጣት ለምን አስፈለገ የሚል ጥያቄ አስነስቷል። ስራ አስኪያጅ የሚሾሙትና የሚያወርዱት ዶ/ር ደብረጺዮን ፣ በህንዱ ኩባንያ ቦታ አቶ ጎሳዬ መንግስቴን በስራ አስኪያጅነት ሹመዋል።
መንግስት የመብራት መቆራረጡን ለመቅረፍ በያመቱ ቃል ቢገባም ሊሳካለት አልቻለም። በመንግስትና በግለሰቦች የተገነቡ የተለያዩ የማምረቻ ፋብሪካዎች በኤሌክትሪክ እጥረት ስራ ሳይጀመሩ ለወራቶች መቀመጣቸውን በተደጋጋሚ ይገልጻሉ።