ኢሳት (ግንቦት 9 ፥ 2008)
ከአንድ አመት በፊት ለእስር የተዳረጉትና በቀረበባቸው የሙስና ወንጀል ክስ በቅርቡ ጥፋተኛ የተባሉት የቀድሞ የሃገር ውስጥ የደህንነት ሃላፊ የአስር አመት ፅኑ እስራት ተላለፈባቸው።
የደህንነት ሃላፊ የነበሩት አቶ ወልደስላሴ ወልደሚካዔል ከተላለፈባቸው የእስር ቅጣት በተጨማሪም የ50 ሺ ብር ቅጣት የተወሰነባቸው ሲሆን፣ ወንድማቸውና እህታቸውም በአራትና በሶስት አመት እስራት መቀጣታቸውንም ከሃገር ቤት የተገኘ መረጃ አመልክቷል።
የደህንነት ሃላፊ የነበሩት አቶ ወልደ ስላሴ በስልጣን በነበሩ ጊዜ ያለ አግባብ ሃብትን አፍርተዋል እንዲሁም ስልጣናቸውን መከታ በማድረግ ህገወጥ ድርጊቶችን ፈጽመዋል ተብለው በቅርቡ የቀረበባቸውን ክስ እንዲከታተሉ ብይን መሰጠቱ ይታወሳል።
ጉዳዩን ሲመለከት የቆየው የፌዴራሉ ከፍተኛው ፍርድ ቤት ማክሰኞ ባልስተላለፈው የፍርድ ቤት ውሳኔም አቶ ወልደስላሴ በ10 አመት ጽኑ እስራትና በ50 ሺ ብር እንዲቀጡ ወስኗል።
ወንድማቸው የሆኑት አቶ ዘርዓይ እና እህታቸው ወ/ሮ ትርሃስ ወልደሚካዔል በሙስና ወንጀሉ ተባባሪ ነበሩ ተብለው እያንዳንዳቸው በአራትና በሶስት አመት የእስራት ቅጣት እንዲሁም የ 20 እና የ 10 ሺ ብር ቅጣት ተላልፎባቸዋል።
ከቀድሞ የደህንነት ሃላፊ ጋር በስድስት ሚሊዮን ብር የሙስና ወንጀል ተጠርጥረው የነበሩት አቶ ዶሪ ከበደ የቀረበባቸው ክስ በበቂ ሁኔታ መከላከል ችለዋል ተብለው በነጻ መሰናበታቸውም ታውቋል።
ከቀድሞ የደህንነት ሃላፊ ጋር በተመሳሳይ የሙስና ክስ ለእስር የተዳረጉትና በቅርቡ የቀረበባቸው ክስ እንዲከላከሉ ብይን የተላለፈባቸው የቀድሞ የገቢዎችና የጉምሩክ ባለስልጣን ሃላፊ አቶ መላኩ ፈንቴ ሰሞኑን የመጨረሻ ፍርድ የሰጣቸዋል ተብሎም ይጠበቃል።
ከአንድ አመት በፊት ከ40 የሚበልጡ ባለስልጣናትና ነጋዴዎች በመመሳጠር ሙስናን ሲፈጽሙ ነበር ተብለው ለእስር መዳረጋቸው የሚታወስ ነው።