(ኢሳት ዲሲ–ግንቦት 15/2010)በሃዋይ ከቀናት በፊት የተከሰተው ኪላዊያ እሳተ ጎሞራ ፍንዳታ በአካባቢው ባለ የከርሰምድር ውሃ ማመንጫ ጣቢያ ላይ ጉዳት ሊያደርስ ይችላል ተባለ።
ከቀን ወደቀን እየተስፋፋ የመጣው ይህ እሳተጎምራ በከርሰ ምድር ሃይል ማመንጫው ላይ የሚደርስ ከሆነ ከባድ ፍንዳታ ከማስከተሉም በላይ አካባቢው በመርዛማ ጋዝ እንዲበከል ያደርገዋል የሚል ስጋትን ማጫሩ ተሰምቷል።
ከዚህም ሌላ የእሳተ ጎመራው ፍንጣቂ ወደ ፓስፊክ ውቅያኖስ እየተወረወረ መሆኑ ደግሞ ሌላ አሳሳቢ ጉዳይ ሆኗል።
ከ19 ቀናት በፊት ነበር የመጀመሪያው የኪላውያ እሳተ ጎሞራ ፍንዳታ በሃዋይ የተከሰተው።
ተደጋጋሚውን የመሬት መናወጥ ተከትሎ የእሳተ ጎሞራው አቅጣጫ ባለመታወቁም 2 ሺ ያህል ነዋሪዎችን ከስፍራው የማሸሽ ሂደት ተካሂዷል።
እሳተ ጎሞራው በተደጋጋሚ ሲፈነዳ መቆየቱንና ማክሰኞ ማምሻውን የፈነዳው እሳተጎመራ ግን በአካባቢው ወዳለው የከርሰምድር ውሃ ማመንጫ ሊደርስ ይችላል የሚለው ስጋት አይሏል።
ከኪላውያ እሳተ ጎሞራ የሚወጣው የአለት ቅላጭ በማመንጫው ላይ የሚደርስ ከሆነ ደግሞ በአካባቢው ከፍተኛ ፍንዳታ እንደሚከሰትና አካባቢውም በመርዛማ ጋዝ ሊሞላ እንደሚችል የሲ ኤን ኤን ዘገባ አመልክቷል።
የአካባቢው የሰልፈር ዳይ ኦክሳይድ መጠን ከእጥፍ በላይ መጨመሩን ያረጋገጡት ተመራማሪዎች የአለቱ ቅላጭ በአካባቢው ወዳለው ፓስፊክ ውቅያኖስ እየገባ እንደሚገኝም አረጋግጠዋል።
የአለቱ ፍንጣቂ ከቀዝቅዛ ውሃው ጋ በሚገናኝበት ጊዜ የሚፈጠረው ግጭት የአካባቢው አየር የመስታወት ስብርባሪ በሚመስሉ ጥቃቅን ነገሮች መሞላቱን ዘገባው ገልጿል።
የእሳተጎሞራው አቅጣጫ እስካሁን ባለመታውቁ ደግሞ ነዋሪዎችን የማሸሽ ሂደቱ ላይ ተጽኖ እንዳሳደረ ዘገባው አመልክቷል።