ሰኔ ፲ (አስር) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም
ኢሳት ዜና:- የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ምክር ቤት ባካሄደው አስቸኳይ ጉባኤ የአማራ ብሔረሰብ ተወላጆች እንዲፈናቀሉ በማድረግ ወንጀል ተጠርጥረዋል ያላቸውን ሁለት የምክር ቤት አባላት የሕግ ከለላ ማንሳቱን አስታወቀ።
የክልሉ ምክር ቤት ምክትል አፈ-ጉባዔ የሆኑት አቶ አቡሽ ሙስጠፋ እንደገለጹት ከሆነ የፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስቴር ያቋቋመው አጣሪ ቡድን ባሰባሰበው መረጃ መሠረት በካማሽ ዞን በያሶ ወረዳ የሚኖሩ በሺህ የሚቆጠሩ የአማራ ብሔረሰብ ተወላጆች መፈናቀል ዙሪያ እጃቸው አለበት በሚል የተጠረጠሩት አቶ ወልተጂ በጋሎ እና አቶ ገርቢ በጊዜ ያለመከሰስ መብታቸው ተነስቷል።
እነኚህ ሁለት የምክር ቤቱ አባላት የካማሽ ዞን ዋና አስተዳዳሪና የዞኑ መንግሥት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ኃላፊ ሲሆኑ፤ ግለሰቦቹ ለክልሉ መንግሥት ሳያሳውቁ ቃለ-ጉባኤ በመያዝ ነዋሪዎቹ እንዲፈናቀሉ አድርገዋል በሚል ተወንጅለዋል።
ይኸው ያለመከሰስ መብታቸው መነሳቱን ተከትሎ በቅርቡም በፍርድ ቤት ክስ ሊመሰረትባቸው እንደሚችል ይገመታል።
የኢሕአዴግ መንግስት በዓለም አቀፍ ደረጃ የደረሰበትን ተቃውሞ ተከትሎ የተፈናቀሉትን ሰዎች ወደነበሩበት ስፍራ እንዲመለሱ መደረጋቸውን ቢገልጽም፣ ወደስፍራው የተመለሱት ሰዎች በተደጋጋሚ እንደሚገልጹት ግን እስካሁን ድረስ የተረጋጋ ህይወት ለመኖር አለመቻላቸውን የቀድሞው የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ጉባኤ የአሁኑ ሰመጉ በልዩ መግለጫው ላይ መጠቀሱ ይታወቃል ሲል ቅዱስ ሀብት በላቸው ከአውስትራሊያ ዘግቧል።