የሁለት ምክትል ጠ/ሚኒስትሮች ሹመት ሕገ መንግስታዊ ድንጋጌን የጣሰ ነው ተባለ

ህዳር ፳ (ሃያ) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-በዛሬው ዕለት የኢትዮጵያ ፓርላማ የሰጠው ተጨማሪ የሁለት ምክትል ጠ/ሚኒስትሮች ሹመት ሕገመንግስታዊ ድንጋጌን
የጣሰ መሆኑን የሕግ ባለሙያዎች አስታወቁ፡፡
በሕገመንግስቱ አንቀጽ 75 ለአንድ ጠ/ሚኒስትር ብቻ ዕውቅና እንደሚሰጥ ያስታወሱት ባለሙያዎቹ በዚሁ አንቀጽ
75(1)ለ ላይ የተመለከተው ጠ/ሚኒስትሩ በማይኖርበት ጊዜ ምክትል ጠ/ሚኒስትሩ ተክቶት ይሰራል የሚለው ንኡስ አንቀጽ አንድ ምክትል ጠ/ሚኒስትር ብቻ  እንደሚኖር የሚያሳይ ነው ይላሉ፡፡በአሁኑ ወቅት ቀደም ሲል የተሾሙትን ጨምሮ ሶስት ምክትል ጠ/ሚኒስትሮች መሾማቸውን ባለሙያዎቹ አስታውሰው ይህ ሕገመንግስታዊ ድንጋጌን የጣሰ አካሄድ ነው ብለውታል፡፡
ጠ/ሚኒስትር ሀይለማርያም እንዲህ ዓይነት ሹመት ለመስጠት ከሕገመንግስቱ በተጨማሪ በአሁኑ ወቅት በስራ ላይ ያለው
የአስፈጻሚ አካላትን እንደገና ለማደራጀት የወጣው አዋጅ ቁጥር 691/2003 ያግዳቸዋል ብለዋል፡፡በዚህ አዋጅ
ክፍል ሁለት አንቀጽ 6 ላይ የሚኒስትሮች ም/ቤት አባላት በሚል የዘረዘራቸው ጠ/ሚኒስትሩን፣ምክትል /ጠ/ሚኒስትሩን፣የሚኒስትር መ/ቤቶችን የሚመሩ ሚኒስትሮች እና በጠ/ሚኒስትሩ የሚሰየሙ ሌሎች ባለስልጣኖች መሆናቸውን ደንግጓል፡፡
ይህው አስፈጻሚ አካላትን እንደገና ለማዋቀር የወጣው አዋጅ አንቀጽ 4 የምክትል ጠ/ሚኒስትሩ ሥልጣንና ተግባር
በሕገመንግስቱ በአንቀጽ 75 የተመለከተው እንደሚሆን በግልጽ አስቀምጧል፡፡
ባለሙያዎቹ ሹመቱ በተለይ ሕገመንግስቱን የጣሰ መሆን እንዳልነበረበት አስታውሰው በዚህ ሹመት መሰረት ጠ/ሚኒስትሩ
በማይኖሩ ጊዜ ማን ይተካቸዋል የሚለው ግልጽ የሆነ ምላሽ የለውም ሲሉ ተችተውታል፡፡
ጠ/ሚኒስትሩ የዚህን ዓይነት ሹመት መስጠት አይችሉም ያሉት ባለሙያዎቹ መስጠት ቢፈለግ እንኳን በቅድሚያ
ሕገመንግስታዊ ማሻሻያ መቅደም ነበረበት በማለት አካሄዱን ነቅፈዋል፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ ሹመቱ በዛሬው እለት እንዲሰጥ የተፈለገው በነገው እለት በኦሮሚያ ምክር ቤት ውስጥ ይነሳል ተብሎ የሚጠበቀውን ውዝግብ ከአሁኑ ለማብረድ መሆኑን ምንጮች ጠቁመዋል።

የኦህዴዱን አቶ ሙክታር ከድርን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር በማድረግ በኦሮሚያ ምክር ቤት ስብሰባ ላይ ነገ ይነሳል ተብሎ የሚጠበቀውን ውዝግብ ለማብረድ ታቅዶ በዛሬው እለት አዲሱ ሹመት ይፋ እንዲሆን መደረጉን የኢህአዴግ ኦህዴድ ምንጮች ገልጸዋል።

ዛሬ በሚጀመረው የኦሮሚያ ምክር ቤት ስብሰባ ላይ፣ የምክር ቤት አባላቱ በአቶ ሀይለማርያም ሹመትና ኦህዴድ ከጨዋታ ውጭ  ሆኗል በሚለው ዙሪያ ከፍተኛ ውዝግብ ይነሳል ተብሎ ይጠበቃል። አዲሱ ሹመት በኦህዴድ ውስጥ ተፈጥሮ የነበረውን ውዝግብ ያርግበው አያርግበው የታወቀ ነገር የለም። ይሁን እንጅ አቶ ደመቀ ምክትል ጠቅላይ ሚኒሰትር ተብለው ከተሾሙ በሁዋላ ሌሎች ተጨማሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒሰትሮች እንዲሾሙ መደረጉ በአራቱ ድርጅቶች ውስጥ ያለውን ፍትጊያ የሚያመላክት መሆኑን ተንታኞች ይናገራሉ።