(ኢሳት ዲሲ–ታህሳስ 19/2010)
በሳውዲ የሚመራው ጥምር ጦር በየመን የሀውቲ አማጽያን ላይ በፈጸመው የአየር ጥቃት ቢያንስ 68 ሰላማዊ ሰዎች በአንድ ቀን ውስጥ መገደላቸው ታወቀ።
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በጎ አድራጎት አስተባባሪ እንደሚሉት ማክሰኞ ዕለት በተከታታይ በተፈጸመው የአየር ጥቃት በአንድ የገበያ ቦታ ላይ በተፈጸመው የመጀመሪያ ጥቃት 54 ሰዎች ሕይወታቸውን ሲያጡ በሁለተኛው ጥቃት ደግሞ 14 ሰዎች መገደላቸው ታውቋል።
የተባበሩት መንግስታት የበጎ አድራጎት ማስተባበሪያ ሃላፊ በጣምራ ጦሩ እየተፈጸመ ያለው ጥቃት ለሰው ልጆች ሕይወት በፍጹም ግድ የማይሰጥ እንደሆነ በሰላማዊ ሰዎች ላይ እየተፈጸመ ያለው ግድያ ማሳያ ነው ብለዋል።
ሃላፊው ጄሚ ማክጎልድሪክ እንዳሉት የመጀመሪያው የአየር ጥቃት በታይዝ ግዛት ሰዎች በሚበዙበት የገበያ ስፍራ የተፈጸመ ሲሆን በዚህም 54 ሰላምዊ ሰዎች ተገድለዋል።
ሁዳይዳ በተባለው ግዛት በተፈጸመው ሁለተኛ የአየር ጥቃት 14 የአንድ ቤተሰብ አባላት ተገድለዋል።
በየመን መንግስት ታማኝ ሃይሎችና በሃውቲ አማጽያን መካከል ባለው ጦርነት በሳውዲ የሚመራው ጥምር ጦር እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በየካቲት 2015 ጣልቃ ከገባ በኋላ ወደ 9 ሺ የሚሆኑ ንጹሃን ዜጎች ሲያልቁ 50 ሺ ያህሉ ደግሞ ቁስለኛ ሆነዋል።
ይህው በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የወጣው መረጃ እንደሚያሳየው ከ20 ሚሊየን በላይ ሰዎች የሰብአዊ እርዳታ ያስፈልጋቸዋል።
ይህም የመንን በአለም ላይ ትልቁ አስቸኳይ የምግብ ዕርዳታ ፈላጊ ሀገር ያደርጋታል።
እየተካሄደ ባለው አሰቃቂ ጦርነት ምክንያት ከሚያልቀው ሕዝብ በተጨማሪ በሀገሪቱ የተከሰተው የኮሌራ ወረርሽኝም የበርካቶችን ሕይወት በመቅጠፍ ላይ ነው።
ከባለፈው መጋቢት ጀምሮ ከ2 ሺ 2 መቶ በላይ ሰዎች በወረርሽኙ ምክንያት ሕይወታቸውን አጥተዋል።
የሃውቲ አማጽያን ባደረሱት ሌላ ጥቃት ደግሞ 32 ሰዎች ሲጎዱ ከዚህ ውስጥ ስድስቱ ሕጻናት መሆናቸው ታውቋል።
አል-ሃይማ በተባለች መንደር ያሉ ሰዎች ያነሱትን አመጽ ለመግታት ነበር የሀውቲ ተዋጊዎች በከባድ መሳሪያ መንደሪቱን የደበደቡት።
ማክሳልድሪክ ኣንደሚሉት ባለፉት 10 ቀናት በተደረገ የአየር ጥቃት በአጠቃላይ 109 የሚሆኑ ሰዎች ሕይወታቸውን አጥተዋል።
አንድ ሺ ቀናቶችን ያስቆጠረው የየመኑ ጦርነት በሳውዲ የሚመራው ጦርም ሆነ የሃውቲ አማጽያን ለሰላማዊ ሰዎች ሕይወት መጥፋት ግድ የሌላቸው ናቸው ይላል የተባበሩት መንግስታት።
ፖለቲካዊ መፍትሄ እንጂ ጦርነት ችግሩን እንደማይፈታውም ይመክራል።