ኢሳት ዜና (ጥቅምት 5፡ 2008)
የፌደራሉ ከፍተኛው ፍርድቤት በሽብርተኛ ወንጀል ክስ፣ የክስ ሂደታቸው በመታየት ላይ የነበሩ አራት ጦማሪያን ከተከሰሱበት የሽብር ወንጀል መከላከል ሳያስፈልጋቸው በነጻ እንዲሰናበቱ ዛሬ አርብ ወሰነ።
በጦማሪያኑ ላይ የመጀመሪያ ዙር ውሳኔውን ይሰጣል ተብሎ የተጠበቀው ፍርድ ቤቱ በጦማሪያኑ ክሳቸውን መከላከል ሳያስፈልጋቸው በአንድ አመት በላይ የቆየው የእስር ጊዜያቸው አብቅቶ በነጻ እንዲሰናበቱ ትዕዛዝ መስጠቱ ታውቋል።
ይሁንና ተከሳሽ በፍቃዱ ሃይሉ ከተመሰረበተ የሽብርተኛ ወንጀል ነጻ ተብሎ አመጽ ቀስቃሽ ናቸው የተባሉ ጹሁፎቹ በወንጀለኛ መቅጫ ህግ እንዲከላከል ፍርድ ቤቱ ውሳኔ መስጠቱን ከሃገር ቤት የተገኘ መረጃ አመልክቷል።
ጦማሪ ናትናኤል ፈለቀ፣ አጥናፉ ብርሃኔ፣ አቤል ዋበላና፣ የክስ ሂደቷ በሌለችበት በመታየት ላይ የነበረው ሶሊያና ሽመልስ የተመሰረተባቸውን የሽብር ወንጀል ክስ መከላከል ሳያስፈልጋቸው በነጻ እንዲሰናበቱ ተወስኗል።
ከወራት በፊት ተመሳሳይ ክስ ቀርቦባቸው የነበሩ አምስት ጋዜጠኞችና ጦማሪያን ክሳቸው እንዲቋረጥ ተደርጎ በነጻ እንዲሰናበቱ መደረጉ የሚታወስ ሲሆን፣ በርካታ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጀቶች የተቀሩ ጦማሪያን በነጻ እንዲሰናበቱ ሲጠይቁ ቆይተዋል።
በዛሬው የፍርድ ቤት ዉሎ የቀረበበት የሽበርተኛ ወንጀል ክስ ተነስቶ ክሱን በወንጀለኛ መቅጫ ህግ እንዲከላከል የተወሰነበት በፍቃዱ ሃይሉ የዋስትና መብት እንዲሰጠው ጥያቄን ቢያቀርብም ፍርድ ቤቱ ጉዳዩን ለመመልከት ለጥቅመት 10, 2008 ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።
ለ38ኛ ጊዜ ፍርድ ቤት ቀርበው የነበሩት ጦማሪያን ለአንድ አመት ከአምስት ወር ያህል ጊዜ በእስር ቤት የቆዩ ሲሆን፣ የመጀመሪያ ዙር ብይን ለማግኘት አምስት ጊዜ ተለዋጭ ቀጠሮ ሲሰጥ መቆየቱ ይታወሳል።
የጦማሪያኑ ጠበቃ የሆኑት አቶ አምሃ መኮንን ደንበኞቻቸው ከጅምሩም ቢሆን ይህን ያህል ጊዜ መታሰር እንደሌለባቸው በመግለጽ ፍርድ ቤት ባቀረበባቸው ክስ በቂ ማስረጃ ሳያገኝ መቅረቱን አስታውቀዋል።
ጦማሪያኑ ሲጽፉት የነበሩ ጹሁፎችም ሃሳብን በነጻነት በመግለጽ የተለየ እንዳልነበርና በሽብርተኛነት የሚያስከስስ አለመሆኑን ፍርድ ቤት ተረድቶታል ሲሉ ጠበቃው አስረድተዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለም የጦማሪያኑ በነጻ መሰናበት አስመልክቶ ቢቢሲ እና የተለያዩ አለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን ሰፊ ሽፋን ሰጥተዋል።
ተከሳሾች ከእስር ቤት እንዲወጡ ትዕዛዝ ቢተላለፍም እስከቅርብ ምሽት ድረስ አለመላቀቃቸው ተውቋል።