ጥር ፳(ሃያ) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-ነገረ ኢትዮጵያ እንደዘገበው ጥር 20 ቀን 2007 ዓ.ም ለ16ኛ ጊዜ በፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 19ኛ ወንጀል ችሎት የቀረቡት ጸሃፊዎች፣ ፍርድ ቤቱ ቀደም ብሎ ተሻሻለ የተባለውን ክስ አይቶ ብይን ሰጥቷል፡፡
የፌደራል አቃቤ ህግ አሻሽየዋለሁ ያለውን ክስ ከአንዱ ነጥብ በስተቀር ሦስቱን መቀበሉን ፍርድ ቤቱ ገልጿል።
በክሱ ላይ ‹ቡድን› በሚል የተጠቀሰው ነጥብ ተከሳሾቹ በህቡ ያቋቋሙት ቡድን መሆኑን ፍርድ ቤቱ ተገንዝቧል ያለው ችሎቱ፣ የቡድኑ አጠቃላይ ሁኔታ በቀጣዩ በክርክር ወቅት በማስረጃ የሚረጋገጥ አልያም ውድቅ ሊሆን የሚችል ስለሆነ በክሱ ላይ መካተቱ ተገቢነቱን ተቀብሎታል ሲል ዘግቧል።
‹‹ተከሳሾች ከ2004 ጀምሮ እጃቸው እስከተያዘበት ጊዜ ድረስ በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገራት በግንቦት 7 አመቻችነት ስልጠና መውሰዳቸውን በተሻሻለው ክስ ተመልክቷል፡፡ ፍርድ ቤቱ የሰጠውን ብይን ተከትሎ ተከሳሾቹ ከጠበቆቻቸው ጋር ተመካክረው በክሱ ላይ ‹‹የእምነት ክህደት ቃል ይሰጡ ከሆነ›› ውሳኔያቸውን እንዲያሳውቁ ለማክሰኞ ጥር 26/2007 ዓ.ም) ችሎት እንዲቀርቡ ውሳኔ አስተላልፏል፡፡