ዝዋይ ከተማ አቅራቢያ የሚገኘው የዝዋይ ሃይቅ በደረሰበት የኬሚካል ብክለት ሳቢያ አደጋ ውስጥ ነው ተባለ

ሚያዚያ ፲፩(አሥራ አንድ) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-በአካባቢው የሚገኙ የአበባ እርሻዎችና ፋብሪካዎች ወደ ሃይቁ በሚደፉት መርዛማ ኬሚካሎች ምክንያት የሃይቁ የአሳ ሃብት እየተመናመኑ መጥተዋል። በያዝነው ዓመት ብቻ ሃይቁ በአሁኑ ወቅት አንድ ሜትር ወደ ታች ወርዷል።የችግሩ አስከፊነት እያሳሰባቸውና እየተባባሰ መምጣቱን የአካባቢው ነዋሪዎች ገልፀዋል።
በአካባቢው ካሉ ገሊላ፣ ደብረሲና፣ደብረፂዮን፣ጠደቻና ፉንድሮ ደሴቶች ነዋሪዎች በተጨማሪ ሌሎችም በአሳ ማምረት ስራ ላይ መሰማራታቸው ከኬሚካሉ ቀጥሎ ሃይቁ ላይ ጉዳት አስከትሏል። ሃይቁ በመበከሉ ምክንያት የዝዋይ ከተማ ነዋሪዎች የመጠጥ ውሃ በመቸገራቸው ቡልቡላ የሚመጣን ውሃ ለአንድ ጀሪካን 15 ብር በመክፈል መጠቀም ግድ ሆኖባቸዋል። አቅም የሌላቸው ገዝተው መጠቀም ስለማይችሉ ለተለያዩ ውሃ ወለድ በሽታዎች መዳረጋቸውን ነዋሪዎቹ ያናገራሉ።
ሃይቁ የቱሪስት መስ ህብ በመሆኑ የባህልና ቱሪዝም ቢሮ ስለጉዳዩ ተጠይቀው ጉዳዩን ሰሚ አካል ማግኘት እንዳልቻሉና ጉዳዩ ከአቅማቸው በላይ መሆኑን የቢሮው ሃላፊ ገልፀዋል።
በኢትዮጵያ የተከለከሉ የግብርና ኬሚካሎች ጥቅም ላይ እየዋሉ መሆኑንና ሃይቁ አደጋ ላይ መሆኑን ሸገር ኤፍ ኤም ዘግቧል።በኢትዮጵያ የተፈጥሮና አካባቢ ጥበቃ ባለመኖሩ በሃረርጌ የአለማያ ሃይቅ መንጠፉ ይታወሳል።